ሁሉም የኢህአዴግ ምክርቤት አባላት ለግንባሩ ሊቀመንበርነት መወዳደር ይችላሉ ተባለ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%88%81%E1%88%89%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%88%85%E1%8A%A0%E1%8B%B4%E1%8C%8D-%E1%88%9D%E1%8A%AD%E1%88%AD%E1%89%A4%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A3%E1%88%8B%E1%89%B5-%E1%88%88%E1%8C%8D%E1%8A%95/

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 21/2010)

ሁሉም የኢህአዴግ ምክርቤት አባላት ለግንባሩ ሊቀመንበርነት መወዳደር እንደሚችሉ አቶ በረከት ስምኦን ገለፁ

ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፅ የተለቀቀው ፅሁፍ ” የእኔ አይደለም” ሲሉም አስተባብለዋል።

ህውሓት/ ኢህአዴግ አጣብቂኝ ውስጥ በገባ ቁጥር ወደ ሚዲያ በመምጣት መግለጫ በመስጠት ይታወቃሉ አቶ በረከት ስምኦን።

የብአዴን ነባር አባልና በተለያዩ የድርጅት እና የመንግስት ስልጣናት ላይ በመመደብ ህውሓትን በታማኝነት ያገለገሉ ናቸው።

በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በውሸትና የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ የሚታወቁት አቶ በረከት ስምኦን ትላንት በቀድሞው የኢትዬጲያ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ድርጅት በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን በመቅረብ በወቅታዊ የድርጅታቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝቡ ያነሳቸው ተቃውሞዎች ምክንያቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠሩ አዳዲስ ማህበራዊ ጥያቄዎችና ፍላጐቶች በመቅረባቸውና በአግባቡ ማስተናገድ ያልተቻለበት ሁኔታ በመፈጠሩ እንደሆነ አቶ በረከት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብን የስርአት ለውጥ ጥያቄ ወደ ማህበራዊ ጥያቄዎች ዝቅ ያደረጉት አቶ በረከት ስምኦን መፍትሔውም እነዚህን ማህበራዊ ጥያቄዎች እየመለሱ መሔድና ማስፋት እንደሆነ አሳስበዋል።

አቶ በረከት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ የሚካሄደው በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በኢህአዴግ ምክርቤት ስብሰባ ብቻ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

የኢህአዴግ ምክርቤት የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በሰጠው ስልጣን መሰረት ተሰብስቦ የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ይመርጣል ብለዋል።

ጥቆማው ከኢህአዴግ ምክርቤት አባላት ውስጥ የሚቀርብ እንደሆነና የተሰጠው ጥቆማ ከፀደቀ በኃላ በሚስጥር ድምፅ ሁሉም የምክርቤት አባላት እንደሚሰጡበት ተናግረዋል።

አቶ በረከት የምክርቤት አባላት ነፃ በመሆናቸው የሊቀመንበር ምርጫው ከውጭ ሆኖ ተጽእኖ ሊያድርበት የሚችል እድል እንደሌለ ገልፀዋል።

ሰሞኑን በእኔ ስም የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠውን ዶክተር አብይ አህመድን ለማጥላላት በማህበራዊ ድረገፅ የተበተነው ፅሁፍ ” የእኔ አይደለም” ሲሉም አስተባብለዋል።

ፅሁፋን በቅድሚያ ያሰራጩትን በደህንነት ቢሮ ደሞዝ የሚከፈላቸው የትግራይ ነፃ አውጪ የማህበራዊ ድረገፅ አስተባባሪዎች መሆናቸው እየታወቀ አቶ በረከት ይሄን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

የህወሃት ማህበራዊ ገጽ ተሳታፊዎች በደህንነት መስሪያ ቤት የሚከፈላቸውን ደሞዝ መጠን በተመለከተ በቅርቡ አንድ ሰነድ ይፋ መሆኑ ይታውቃል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.