ህብረተሰቡ በችግር ወቅት ያዳባረውን የመተባበርና የመደገፍ እሴት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህብረተሰቡ በችግር ወቅት ያዳባረውን የመተባበርና የመደገፍ እሴት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ።

በሃዋሳ ከተማ በሰብዓዊ ድጋፍና ልማት ላይ የሚንቀሳቀሰው “ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በከተማዋ ባለሃብቶችንና ድርጅቶችን በማስተባበር በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ ለሚገኙ አ1 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት ተግባር አከናውኗል።

ድጋፉ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፥ በኮቪድ-19 ምክንያት ኑሯቸው ላይ ተፅዕኖ የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ያደረገ ነው።

“ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን” የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት፣ አሰልጥኖ በአነስተኛ ቢዝነስ
የማሰማራትና በፍላጎታቸው ላይ ተንተርሶ ወደ ቤተሰብ የመመለስ ተግባርም ያከናውናል።

አምስቱን የጳጉሜ ቀናት የመረዳዳት ሳምንት በሚል በሃዋሳ ከተማ አቅመ ደካሞችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የመጠየቅ መረሃ ግብር ተጀምሯል።

በሃዋሳ ከተማ በ2012 ዓ.ም 1 ሺህ 300 የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና በማንሳት ወደመደበኛ ህይወት እንዲመለሱ መደረጉን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው አቶ ጥራቱ፥ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመትም የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማዕከል አስገብቶ የህይወትና የክህሎት ስልጠና በመስጠት የስራ ዕድል ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን በመደገፍ የጎዳና ተዳዳሪነትን ለመቀነስም መሰል ትብብሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች የፀጥታ ስጋት ሳይሆኑ ሰብአዊ እርዳታ ቢያገኙ በሃገር ልማት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ሰዋዊ ሃብት መሆናቸውን ገልፀዋል።

በማህበራዊ ቀውስ ምክንያት በጎዳና የሚገኙ ወገኖችን ማንሳት ብቻ ሳይሆን አሰልጥኖ የስራ ዕድል መፍጠር ይገባልም ብለዋል።

በዚህም “ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን” ከከተማዋ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ላበረከተው ድጋፍ በከተማው አስተዳደር ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሶዶ ለማ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

The post ህብረተሰቡ በችግር ወቅት ያዳባረውን የመተባበርና የመደገፍ እሴት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- የሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply