ህወሓት ከውጭ አገራት ጋር የሚያደርገውን ኢ-ህገመንግሥታዊ ግንኙነት ማጋለጥ እንደሚገባ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ…

ህወሓት ከውጭ አገራት ጋር የሚያደርገውን ኢ-ህገመንግሥታዊ ግንኙነት ማጋለጥ እንደሚገባ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ህወሓት ከውጭ አገራት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ድርጊት ኢ ህገመንግሥታዊ መሆኑንና ከዚህ አካል ጋር የሚተባበር ማንኛውም አካል የወንጀሉ ተባባሪ መሆኑን ለዓለም አገራት ማሳወቅ እንደሚገባ የህግ ምሁራን ገለጹ። አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የህግ ምሁራን እንዳብራሩት፤ ህወሓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በመጣስ ያደረገው ምርጫ ኢ- ህገመንግሥታዊ መሆኑ እየታወቀ የፌዴራል መንግሥቱን ስልጣን በመውሰድ ከውጭ አገራት እያደረገ ያለው ግንኙነት በዓለም አቀፍ ህግም ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም የዓለም አገራት ከህወሃት የሚደረግላቸውን ማንኛውንም ጥሪ መቀበል እንደማይገባቸውና ይህን ካደረጉም የኢ-ህገመንግሥታዊ ተግባሪ ተባባሪ እንደሆኑ ማሳወቅ ያሻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ እንደተናገሩት፤ ህገመንግስቱ አንቀፅ 50 ንዑስ ቁጥር 8 ላይ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ስልጣን በህገመንግስቱ የተወሰነ መሆኑን ይደነግጋል። እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የክልሎችን እንዲሁም ክልሎች የፌዴራል መንግሥትን ስልጣን ማክበር እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ከዚህ አንፃርም የትግራይ ክልል መንግሥት ሰሞኑን ያደረገው ምርጫም ሆነ ከተለያዩ አገራት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት የህገመንግሥቱን ድንጋጌዎች በግልፅ የሚጥስ ነው። «የህገመንግሥቱ የተለያዩ ድንጋጌዎች ፖለቲካዊ መብቶችንም ሆነ የውጭ ግንኙነት አስመልክቶ ለፌዴራል መንግሥት ነው የተሰጠው» ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ እውቅና ውጭ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ማንኛውም ህጋዊ አማራጭ አለመኖሩን አስረድተዋል። ይህ እየታወቀ ግን የትግራይ ክልል መንግሥት በተለያየ ጊዜያት ለዓለምአቀፍ ተቋማት የፌዴራል መንግሥቱን የሚወነጅል ሃተታ በመፃፍ የአገርን ስም የሚያጎድፉ ተግባራት ሲፈፅም መቆየቱን አስታውሰዋል። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ህግን በይፋና በማናለብኝነት በመጣስ ከክልል መንግሥትነት ወደ ህገወጥ ቡድንነት መሸጋገሩን አመልክተዋል። ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኘት ሲል ከአገራት ጋር ህገወጥ ግንኙነት ያደርግ እንደነበር ዶክተር ሲሳይ አስታውሰው፤ ሰሞኑንም በክልሉ የተካሄደውን ህገወጥ ምርጫ እንዲታዘቡለትና እንዲዘግቡለት ለተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችና ጋዜጠኞች ያደረገው ጥሪ እውቅና ለማግኘት ከማለም ባለፈ በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጫና ለመፍጠር የታቀደ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህ ተግባሩ የአገሪቱን ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች የጣሰ ብሎም በዓለምአቀፍ ግንኙነት መርህም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ «ህውሃት በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአገሪቱ ላይ ይሄነው የሚባል ተፅእኖ አያመጣም» ያሉት ዶክተር ሲሳይ ይሁንና ድርጊቱ ኢ-ህገመንግሥታዊ በመሆኑና በዚህ ደረጃም መቀጠል ስለማይገባው የፌዴራል መንግሥቱ ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በተለይም ከህወሓት ጋር የሚደረግ ማንኛውም መንግሥታዊ ግንኙነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት ሊያሻክርባቸው እንደሚችል ማስገንዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል። የህግ አማካሪና ተንታኝ አቶ ዝናቡ ይርጋ በበኩላቸው ህገመንግስቱ በአንቀፅ 46ና 47 የክልሎችን ስልጣን ገደብ በግልፅ የሚያስቀምጥ መሆኑን ጠቁመዋል።«በዚህ ድንጋጌ መሰረት ትግራይ ክልል እንጂ አገር አይደለችም። የፌዴራል መንግሥቱም የአገራት ስብስብ ሳይሆን በክልሎች የተዋቀረ መሆኑንም አመልክተው፤ በመሆኑም የትግራይ ክልል መንግሥት የራሱን ምርጫ ቦርድ ከማቋቋም ጀምሮ የውጭ የምርጫ ታዛቢዎችንና ጋዜጠኞችን መጋበዝ ብሎም በተለያዩ አገራት እውቅና እንዳለው መንግሥት ሆኖ ፅህፈትቤት ለማቋቋም የሚያደርገው ጥረት በየትኛውም አግባብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አብራርተዋል። እንደአቶ ዝናቡ እምነትም፤ የውጭ አገራት ከፌዴራል መንግሥቱ እውቅና ውጭ ከትግራይ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያፈርስ ነው። ህገመንግሥትን ጥሶ አገር ነኝ ከሚል ክልል ጋር የሚደረግ ግንኙነትም የወንጀለኛ ተባባሪ ከመሆን ተለይቶ አይታይም።በመሆኑም ይህንን ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እዚህ ላሉት ኤምባሲዎችም ሆነ ውጭ ባሉት ቆንፅላዎች አማካኝነት ለአገራቱ በግልፅ ማሳወቅ ይገባዋል። በሌላ በኩልም በአሁኑ ወቅት ሕወሓት የፌዴራል መንግስት ህግ የማስከበርም ሆነ የማክበር ግዴታውን ወደ ጎን በመተው በክልሉ ትግሬ አይደለንም በሚሉ ህዝቦች ላይ እያደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በዓለምአቀፍ ህግ ተጠያቂ እንደሚያደርገው አቶ ዝናቡ አስገንዝበዋል። «ትግሬ አይደለንም በሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየተፈፀመ ነው ያለው። በተለይም በራያ፤ ወልቃይት ጠገዴ፥ ሁመራ ባሉ የአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየተፈፀመ ነው፤ በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱ በአገሪቱ ህግም ሆነ በዓለምአቀፍ ህግ ተጠያቂ ሊያደርገው ይገባል» ሲሉ ተናግረዋል። አዲስ ዘመን መስከረም 2/2013

Source: Link to the Post

Leave a Reply