ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአኵስም ጉብኝት መስተጓጎል: የመንግሥት አመቻች አካልና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በየበኩላቸው የሰጡት ምላሽ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/01/12/%E1%88%88%E1%89%A5%E1%8D%81%E1%8B%95-%E1%8B%88%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A1%E1%8A%90-%E1%88%98%E1%88%AD%E1%89%86%E1%88%AC%E1%8B%8E%E1%88%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8A%B5%E1%88%B5/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/01/fb_img_1547286598426.jpg

fb_img_1547286598426

 • “ተጠያቂው የትግራይ ክልል ሳይኾን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፤ከዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጀምሮ ጉብኝቱን ለማመቻቸት ክልሉ ፈቃደኛና ዝግጁ ነው፤ አኵስሞችም ቅዱስነታቸው ከውጭ ከተመለሱ ጀምሮ ኮሚቴ አቋቁመውና ጥሪ አቅርበው ጉብኝታቸውን ሲጠባበቁ ነበር፤”/የጉብኝቱ አመቻች መንግሥታዊ አካላት/
 • “የጎንደሩን ጉብኝት ያመቻቹት የቅዱስነታቸው ቤተሰቦች ናቸው፤ በቤተሰቦቻቸው እጅ ነው ያሉት፤ የአየር ትኬት እገዛለሁ፤ አበል እከፍላለሁ፤ትራንስፖርት አመቻቻለሁ፤ የእኔ ድርሻ ይህ ነው፤ ለአኵስሙ ጉዞ ግን ሓላፊነት ወስዶ ደብዳቤ ጽፎ ያመጣልኝ ማንም የለም፤” /ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ/
 • “ፓትርያርክ እኮ ተቋምም ነው፤ ክፍተቱ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ለፓትርያርክ በሚገባ ደረጃ ካለመቀበል የሚመነጭ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የትኩረት ማነስ ነው፤ የሚሌኒየም አዳራሹ የድጋፍ አቀባበል ጊዜ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንኳ፣ ወጪው ተጠንቶ ይቅረብልንና እንወስን፤ ሲሉ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ግን፣ ተገቢ በጀት ባለመመደብ ንፉግነቱን ከአቀባበላቸው ቀን ጀምሮ በግልጽ አሳይቷል፤ በተለያየ መልክ የቀጠለውም ይኸው የትኩረት ማነስ ነው፤” /አስተያየት ሰጭዎች/
 • ቅዱስነታቸው ፕትርክና እንደተሾሙ አኵስም ሔደው በጸሎታችሁ አስቡኝ ብለው መባ ሰጥተዋል፤የአኵስም ጽዮን ካህናትም ማንም የቅዱስነታቸውን ስም በማይጠራበት በዚያ በመከራ ዘመን በጸሎተ ቅዳሴ ከማሰብ ያላስታጎሉ ናቸው፤ አሁንም ቅንነቱ ካለ ከጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ታቦር ጉብኝት በኋላ የአኵስሙን ጉብኝት ለማመቻቸት የሚያግድ ነገር የለም፤ መንግሥትም የሚያስፈልገውን ነገር ኹሉ ሊያሟላ ይችላል፤ /የጉብኝቱ አመቻቾች/

***

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ራብዓይ

ራብዓይ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያ የኾነውን አባታዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ቅዳሜ፣ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ጎንደር ከተማ ገብተዋል፡፡ በካህናት፣ ሊቃውንት፣ ምእመናንና በከተማው አስተዳደር ሓላፊዎችም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በጎንደር በድምቀትና በልዩ ኹኔታ ከሚከበረው የጥምቀት በዓል አከባበር ጋራ የተገናኘ ጉዞ እንደኾነና በይዘቱም የሰላምና የስብከተ ወንጌል ተልእኮ እንዳለው በቅርብ ረዳቶቻቸው ተገልጿል፡፡ ጉዟቸውን ከአኵስም እንዲጀምሩ ታቅዶ ለክልሉ አካላት ጥያቄ መቅረቡንና ተገቢ ዝግጅት አድርጎ ለመቀበልና ለማስተናገድ ግን ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመሰጠቱ የቅዱስነታቸው የጎንደር ጉብኝት ዘግይቶ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡


በአንጻሩ፣ የቅዱስነታቸው ጉብኝት የታሪክና የካህናት ከተማ ከኾነችው ርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቢጀመር፣ ለሰላሙም፣ ለፍቅሩም ለሕዝቦች አንድነትም የተሻለ ነው፤ በሚል ሲንቀሳቀሱ የቆዩ መንግሥታዊ አካላት፣ ለመርሐ ግብሩ መስተጓጎል ተጠያቂው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንጂ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንዳልኾነ በመግለጽ በቀደመው ዘገባ የተላለፈው መረጃ እርማት እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

ከኹሉ በፊት፣ ቅዱስነታቸው ከስደት እንደተመለሱ፣ አኵስምን አስቀድመው እንዲጎበኙ የጠየቁት የጽዮን ማርያም ካህናት እንደኾኑ አውስተው፣ የአቀባበል ኮሚቴ አቋቁመው አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት እንደጠየቋቸው ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታም፣ በሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ኂሩት ካሰው ጥያቄው መቅረቡን፣ በኋላም ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደርሶ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋራ ተነጋግረው ፈቃዱና ዝግጁነቱ ተረጋግጦ አቀባበሉ በክልል አቀፍ ደረጃ ይኾን ዘንድ በትብብር ለመሥራት ኹኔታዎች ተመቻችተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ይህም ለፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ልዩ ጽ/ቤት እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተነግሮ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ደብዳቤ እንዲጽፉ በጉብኝቱ አመቻቾች ጥያቄ ቢቀርብም፣ “እኔ አያገባኝም፤ ይህ ጉዳይ እኔን አይመለከተኝም፤ ከዚህ ሒደት አውጡኝ፤” በማለት ለመተባበር ፈቃደኛ እንዳልኾኑ ሒደቱን በቅርበት የተከታተሉ አካላት አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ስናናግር የቅዱስነታቸውን ቤተሰቦች አናግሩ፤ ይላሉ፤ ቤተሰቦቻቸውን ስናናግር ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን አናግሩ ይላሉ፤ ችግሩ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም አይደለም፤ ዋናው ተጠያቂው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዮስቆሮስ ናቸው፤” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

“ቅዱስነታቸው ፕትርክና እንደተሾሙ አኵስም ድረስ ሔደው በጸሎታችሁ አስቡኝ ብለው መባ ሰጥተዋል፤ የአኵስም ጽዮን ካህናትም ማንም የቅዱስነታቸውን ስም በማይጠራበት በዚያ በመከራ ዘመን በጸሎተ ቅዳሴ ከማሰብ ያላስታጎሉ ናቸው፤ ከአኵስም ጽዮን ክብርና ከቅዱስነታቸው ጉብኝት ታሪካዊነት አንጻር ጉብኝታቸው ለሰላም፣ ለፍቅርና ለሕዝቦች አንድነት ያለውን ፋይዳ ተገንዝቦ መርሐ ግብሩ እንዲሳካ ድጋፍ አለማድረግ፣ ለሰላም ተልእኮ በሚሊዮኖች መድቤያለሁ፤ ሰባክያንን አሠልጥኜ በኹሉም አህጉረ ስብከት አሰማርቻለሁ፤ ከሚል አካል እንደማይጠበቅ ተችተዋል፤ እኚህ ፓትርያርክ ከሰባክያን አይበልጡምን? ሰላምን ተቀበሏት ብሎ ከመስበክ ይልቅ ሰላምን ሲቀበሏት አየን ማለት አይበልጥም? አይደለም በሌላ አካል ተጠይቀው፣ ፓትርያርኩ ራሳቸው አይሏቸውም እንጂ አልችልም ቢሏቸው እንኳ ለምነው፣እግራቸው ሥር ወድቀው እንዲሔዱ ማድረግ ነው ያለባቸው፤” በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ለጉብኝቱ አመቻች አካል የሚጠበቀውን ያህል ድጋፍና ተነሣሽነት እንዳላሳዩ አማረዋል፡፡

ለቅዱስነታቸው ጤናም ኾነ ደኅንነት ከመንግሥት ተፈላጊውን ድጋፍ መጠየቅና እንዲሟላ ማድረግ እየተቻለ፣ ከዚህ አንጻርም የሚቀርበው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ስጋት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ እንኳንስ ወደ አኵስም መሔድ ከአሜሪካ ድረስ መጥተዋል፤ ያሉት አመቻቾቹ፣ አሁንም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቅንነቱ ካለው ከጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ታቦር ጉብኝታቸው በኋላ የአኵስሙን ጉብኝት ከማመቻቸት የሚያግደው ነገር እንደማይኖር አመልክተዋል፡፡

papase-265x198የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በበኩላቸው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተቋም እስከኾነ ድረስ የሚጠየቀው ነገር ኹሉ ሓላፊነት በሚወስድ አካል በጽሑፍ መቅረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል፤ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የአኵስም ጉዞ በተመለከተ፣ የጉብኝቱ አመቻቾች ነን ያሉ አካላት ዘግይተው በቃል ከጠየቁት ውጭ ሓላፊነት ወስዶ ደብዳቤ ጽፎ ያቀረበላቸው ማንም አካል እንደሌለ በመጥቀስ ወቀሳውንና ተችቱን ተከላክለዋል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዕለታዊ መርሐ ግብርም ኾነ እንቅስቃሴ የሚወሰነው፣ በቤተሰቦቻቸው ነው፤ ያሉት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ድርሻ፣ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል፣ በጀትና ተሽከርካሪ ሲጠየቅ ማሟላት እንደኾነ ጠቁመዋል፤ ለጎንደሩም ጉብኝት የአየር ትኬት፣ የውሎ አበልና ትራንስፖርት ከማመቻቸት ውጭ እንደ ሥራ አስፈጻሚ አካል በፓትርያርኩ የጉብኝት ቅደም ተከተል ላይ የመወሰን ሥልጣኑ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ፣ “የአኵስም ጉብኝት ይቅደም” ጥያቄ፣ በአመቻቾች የተነገራቸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ እንደኾነና ይህም የቅዱስነታቸው የጎንደር ጉብኝት በቤተሰቦቻቸው ተወስኖ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ከተከናወነ በኋላ በሦስት ሳምንት የዘገየ በመኾኑ የመርሐ ግብር ማስተካከያውን አዳጋች እንዳደረገው ጠቅሰዋል – “በቤተሰቦቻቸው ጥያቄ ለክልሉ መንግሥት ደብዳቤ ተጽፎ ከተላከና ለጉዞው ትኬት ከተቆረጠ ከሦስት ሳምንት በኋላ ነው እነ አቶ አምሃ እና ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ትላንትና እና ከትላንት ወዲያ መጥተው፣ አስቀድመው ወደ አኵስም እንዲሔዱ መርሐ ግብር ይያዝ ተብሏልና ለአኵስም ደብዳቤ ይጻፉልን፤ ያሉኝ፤ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ጎንደርም፣ ባሕር ዳርም፣ ደብረ ታቦርም ቀድመን መርሐ ግብር ይዘናል፤ ፕሮግራም ከተያዘ በኋላ መሰረዝ ከሕዝብ ጋራ መጣላት ነው፤ አሉ፤ እኔም፣ እንግዲያው ካልተስማማችሁ ምንም ማድረግ አልችልም ብዬ በተጠየቅኹት መሠረት ፈጽሜያለሁ፡፡ ሓላፊነት ሊሰጠኝ የሚችል አካል በደብዳቤ ሲጠይቀኝ የአየር ትኬት እገዛለሁ፤ የውሎ አበል እከፍላለሁ፤ ትራንስፖርት አመቻቻለሁ፤ የእኔ ድርሻ ይኸው ነው፤ በዚህ ወይም በዚያ ይሒዱም አልልም፤ አይሒዱም አልልም፤ እንዲህ የማዘዝ ሥልጣኑም የለኝም፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

merkoreos-ze-ethiopia-1

በሌላ በኩል፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአኵስም ጉብኝት መስተጓጎል የታየው ክፍተት፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ ቅዱስነታቸውን በመዋቅር ደረጃ ለመቀበል ከጅምሩ የነበረበትንና ከዚያም በኋላ የቀጠለውን የትኩረት ክፍተት እንደሚያሳይ የተናገሩ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው፣ ልዩ ጽ/ቤታቸውን በወጉ አቋቁሞ፣ በፓትርያርክ ደረጃ የሚገባቸውን በጀትና የሰው ኃይል አሟልቶ ከማስተናገድም አንጻር በርካታ ችግሮች እየታዩ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ልዩ ጽ/ቤቱ በቅጡ ቢደራጅ ኖሮ፣ የጉብኝቱ ቅደም ተከተልና ዝግጅቱ በአግባቡና በወቅቱ ሊታቀድ ይችል እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡

“ፓትርያርክ እኮ ተቋምም ነው፤ አሁን የጉብኝቱን መስተጓጎል ምክንያት አድርጎ የታየው ክፍተት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ለፓትርያርክ በሚገባ ደረጃ ካለመቀበል የሚመነጭ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የትኩረት ማነስ ነው፤ የሚሌኒየም አዳራሹ የድጋፍ አቀባበል ጊዜ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንኳ፣ ወጪው ተጠንቶ ይቅረብልንና እንወስን፤ ሲሉ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ግን፣ ተገቢ በጀት ባለመመደብ ከአቀባበላቸው ቀን ጀምሮ ንፉግነቱን በግልጽ አሳይቷል፤ ከዚያም በኋላ በተለያየ መልክ የቀጠለውም ይኸው የትኩረት ማነስ ነው፤” በማለት የችግሩ ዋነኛ መንሥኤ ነው ያሉትን አብራርተው የበለጠ ከመወሳሰቡ በፊት አፋጣኝና ኹነኛ መፍትሔ እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡  

ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ግን ይህንም አስተባብለዋል፡፡ መዋቅራዊነትን በተመለከተ ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት፣ ባለፈው ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፡-

 • አቡነ ቀሲስ
 • ፕሮቶኮል
 • ነርስ ከትርፍ ጊዜ አበል ጋራ
 • ሹፌር እና መኪና
 • መነኰሳት ልዩ ረዳቶች
 • ምግብ አብሳይ(ወጥ ቤት)
 • የተሟሉ የቤት ዕቃዎች

የቅዱስነታቸው ቤተሰቦች ራሳቸው መርጠው ላቀረቧቸው መነኰሳት እና ባለሞያዎች ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቅጥር መፈጸሙን አስታውቀዋል፤ ከተመለሱበት ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አንሥቶም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እኩል ወርኃዊ ደመወዝ፣ አበል፣ የምግብና መስተንግዶ በጀት መመደቡን ተናግረዋል፤ ከዚህም በላይ የሚያስፈልግ ተጨማሪ ወጪ ካለ በሥርዓቱ ሲቀርብላቸው ምላሽ እንደሚሰጡ ቤተሰቦቻቸውን ሰሞኑን ሰብስበው እንዳስታወቁ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአኵስም ጉብኝት ቢቀድም በሚል ለማመቻቸት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አካላት የተሰጠ አስተያየት በዝርዝር

ከመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች በሚል በዘገባው የተላለፈው መረጃ የተሳሳተ ነው፤ መታረም አለበት፤ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአኵስም ጉብኝት መስተጓጎል የትግራይ ክልል ተጠያቂ መደረጉ ስሕተት ነው፡፡ ትልቁን ስሕተት የሠሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ናቸው እንጂ የክልሉ አካላት አይደሉም፡፡ ጉብኝቱን ለማመቻቸት በተደረገው ጥረት ስለነበርንበት ሒደቱን እናውቃለን፡፡ የክልሉን ም/ል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልንም አናጋግረነዋቸዋል፡፡

dr debretsion gebramichaelከኹሉ በፊት፣ የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ማርያም ካቴድራል አስተዳደርና ማኅበረ ካህናት የአቀባበል ኮሚቴ ካቋቋሙ ቆይተዋል፡፡ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ መጥተው፣ ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስን፣ እንኳን ደኅና መጡ፤ ብለው አኵስምን እንዲጎበኙ በክብር ጠይቀዋቸዋል፤ የአቀባበል ኮሚቴው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተዘጋጅቶ እየተጠባበቀ ነበር፤ ነገር ግን ቆይቶ፣ መጀመሪያ ጎንደር ነው የሚሔዱት የሚባል ነገር ሲሰማ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ካሰው፣ ጉብኝቱ ከአኵስም ቢጀመር ለሰላሙም፣ ለፍቅሩም ለሕዝቦች አንድነትም የተሻለ ነው፤ አስፈላጊውን ነገር እናሟላ፤ ብለው ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ኾኖም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ስናናግር የቅዱስነታቸውን ቤተሰቦች አናግሩ፤ ይላሉ፤ ቤተሰቦቻቸውን ስናናግር ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን አናግሩ ይላሉ፤ በመሀል ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮም ደርሶ ነበር፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚሁ ጉዳይ ከም.ል ርእሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋራ ተነጋግረዋል፤ ለአቀባበሉ አስፈላጊው ነገር ተሟልቶ በክልል ደረጃ እንዲደረግ ሲጠይቋቸው ም/ል ርእሰ መስተዳድሩ በደስታ ተቀብለውት ለሚመለከታቸው መመሪያ ሰጥተዋል፤ ለአኵስሞችም ሲነግሯቸው፣ እኛ ኮሚቴ አዋቅረን ተዘጋጅተን እየጠበቅናቸው ነው፤ መመሪያ የሚሰጠን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ስለኾነ፣ ደብዳቤ ባይጽፍ እንኳን በዚህ ቀን ይመጣሉ፤ ተቀበሏቸው ቢለን እኛ ዝግጁ ነን፤ ነው ያሏቸው፡፡

ይህም ጉዳይ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ልዩ ጽ/ቤት እና ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጁም ተነግሯል፤ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ግን፣ “እኔ አያገባኝም፤ ይህ ጉዳይ እኔን አይመለከተኝም፤ ከዚህ ነገር ወጥቻለሁ፤ ደብዳቤም አልጽፍም፤ ምንም አላደርገም፤” ብለው ዝም አሉ፡፡ ይህን የሚሉበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እንዲያውም ራሳቸው ገፍተው፣ ቅዱስነትዎ ቢሔዱ፤ ብለው መለመን ነው ያለባቸው፤ አንዱ የሰላም ስምሪት ይኼ አይደለም ወይ? ለሰላም ተልእኮ 9 ሚልየን ብር መድበን በየቦታው ስለ ሰላም እንዲብኩ ሰባክያንን ልከናል፤ ብለዋል፡፡ እኚህ ፓትርያርክ ሰባክያንን አይበልጡም፤ ከ9 ሚሊዮን ብሩስ 5 ሚሊዮን ብር ቢመደብ ትልቅ ውጤት የሚያመጣው ይኼ አይደለም ወይ? አቀባበል አድርገው ስለ ሰላም ሲሰብኩ ብናሳይ አይሻልም? ሰላምን ተቀበሏት ብሎ ከመስበክ ሰላምን ሲቀበሏት አየን ማለት አይበልጥምን? ፓትርያርኩ እምቢ፣ አልችልም ቢሏቸው እንኳ ለምነው፣ እግራቸው ሥር ወድቀው እንዲሔዱ ማድረግ ነው ያለባቸው፤

አኵስሞች የአቀባበል ኮሚቴ አቋቁመው እዚህ አዲስ አበባ ድረስ ተሰብስበው መጥተው፣ ይጎብኙን ብለው ጠይቀዋቸዋል ቅዱስነታቸውን፤ ክልላዊ መንግሥቱም ፈቃደኛና ዝግጁ ኾኗል፤ እውነት ለመናገር፤ በዚህ ዶ/ር ደብረ ጽዮን በጭራሽ ሊወቀሱ አይችሉም፤ ፈቃደኛና ደስተኛ መኾናቸውን በቃላቸው ሲናገሩ ሰምተናቸዋል፤ “በአካል ሔጄ እኮ አይቻቸዋለሁ፤ ደስተኛ ነኝ፤ እንዲመጡ በጣም ነው የምንፈልገው፤ የሚመጡት ወደ አኵስም ስለኾነ ለሚመለከታቸው ነግሬያለሁ፤ምን ተጨማሪ ነገር እንደሚያስፈልግ ይነገረንና ፓትርያርኩ ወይም ልዩ ጽ/ቤታቸው ቢደውሉልን የሚያስፈልገውን ደግሞ እንጨምራለን፤ ምን ምን መደረግ እንዳለበት በዝርዝር አናውቅም፤ ለአኵስም ጽዮን መመሪያው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ይድረሳቸው፤ በእኛ ሳይኾን በእነርሱ ነው መታዘዝ ያለባቸው፤” ነው ያሉት፡፡ አላስፈላጊና እውነት ባልኾነ ነገር ለምን ስም ይጠፋል? በምንም መልኩ የእነርሱ ስሕተት አይደለም፡፡ ለብፁዓን አባቶች ዕርቀ ሰላም ሲንቀሳቀሱ የነበሩት እነአቶ አምሃ ሁሉ ለፍተዋል፤ አቡነ ዲዮስቆሮስን ለምነዋቸዋል፤ ችግሩ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስም፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም አይደለም፤ ዋናው ተጠያቂው ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዮስቆሮስ ናቸው፤ ነው የምንለው፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሰጡት ምላሽ

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽቤት ዋና ሥራ አስስለ እኔና ስለ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተባለው ከእውነት የራቀ ሐሰት ነው፤ በመጀመሪያ ቅዱስ ፓትርያርኩ በቤተሰቦቻቸው እጅ ነው ያሉት፤ እንደ እርሳቸው ኹነው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ተቋሙን ማለትም እኛን ጠቅላይ ጽ/ቤቱን የሚጠይቁት ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ ደብዳቤ ጽፈው፣ ወደ ጎንደር እንሔዳለን፤ የአየር ትኬት፣ ትራንስፖርት፣ አበል ይፈቀድልን ብለው ለእኔ አመለከቱ፤ እኔም መልካም ነው ብዬ ለቅዱስነታቸው፣ አብረዋቸው ለሚጓዙ ብፁዓን አባቶችና ረዳቶቻቸው የጠየቁትን ፈቀድኩ፤ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ከአሜሪካ የመጡት ብፁዕ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ በርናባስ አብረዋቸው አሉ፤ እኔንም ብፁዕ ዋና ጸሐፊውንም መዝግበውን ነበር፤ ስላልተመቻቸ አልሔድንም፤ ቤተ ሰዎቻቸው ይኼን የጠየቁኝ ከሦስት ሳምንታት በፊት ነው፤ ከዚያ በኋላ ትላንት እና ከትላንት ወዲያ(ኀሙስ እና ዓርብ) ነው እነአቶ አምሃ፣ መጀመሪያ አኵስም ነው መሔድ ያለባቸው ብለው የጠየቁኝ፤ “ዶ/ር ዐቢይ አስቀድመው ወደ አኵስም እንዲሔዱ መርሐ ግብር ይያዝ ብለዋል፤ደብዳቤ ይጻፉ ለአኵስም አለኝ፤” አለኝ፤ ብርሃኑ አድማስም፣ ዝግጅት እንዳለ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ እንደተነገራቸውና ጉዟቸውም መጀመሪያ አኵስም ከዚያ ጎንደር እንዲኾን መጠየቃቸውን ነገረኝ፤ በቤተ ሰዎቻቸው ጥያቄ ትኬት ተቆርጦ፣ ለክልሉ[ለአማራ] መንግሥት እና ለጎንደር ማዕከላዊ ዞን ደብዳቤ ተጽፎ ከተላከ በኋላ ማለት ነው፡፡

እኔም፣ ይኼ እኔን አይመለከተኝም፤ ይሒዱም አልልም፤ አይሒዱም አልልም፤ ጠያቂ አካል ያስፈልጋል፤ የቅዱስነታቸውን ፍላጎት፣ የት እንደሚሔዱ፣ የት እንደሚውሉ፣ የት እንደሚያድሩ፣ ምን እንደሚበሉ ሓላፊነት ወስደው እየሠሩ ያሉት ቤተ ሰዎቻቸው ናቸው በዙሪያቸው ኹነው፤ አሁንም ሓላፊነት ወስዶ ይኼ ይኼ ይደረግ ብሎ በጽሑፍ የሚጠይቀኝ ካለ፣ የቤተ ክርስቲያን አባት ናቸው፤ የአየር ትኬት እገዛለሁ፤ አበል እከፍላለሁ፤ትራንስፖርት አመቻቻለሁ፤ የእኔ ድርሻ ይህ ነው፤ ሓላፊነት የሚሰጠኝ አካል ወይም ቤተ ሰዎቻቸው በደብዳቤ ይጠይቁኝ፤ እኔ አመቻቻለሁ፤ በራሴ ሥልጣን ግን ማዘዝ አልችልም አልኹት፡፡

ፓትርያርክ ናቸው፣ በዚህ ወይም በዚያ መሔድ አለባቸው ብዬ ማለት አልችልም፤ አደጋ ቢፈጠርና አንድ ነገር ቢኾኑ ተጠያቂ እንደምኾን ለራሴ አውቀዋለሁ፤ ጉንፋን እንኳ ቢይዛቸው ተጠያቂነት አለ፤ ማንም ሰው መግባት አይችልም፤ ሕመምተኛ ናቸው፤ መናገርም ብዙም አይናገሩም፤ትልቅ ፈተና ነው፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው፤ እናንተ ከቤተ ሰዎቻቸው፣ ከፕሮቶኮላቸው ጋራ ተነጋገሩ፤ ተስማሙ፤ አንድ ድምፅ ኹኑ፤ መጀመሪያ አኵስም እንሒድ ካሉ ደብዳቤ ይምጣልኝ፤ በደብዳቤው መሠረት የአየር ትኬት እገዛለሁ፤ አበሉን፣ ትራንስፖርቱን አመቻቻለሁ፤ ከዚህ ውጭ ግን ወደዚህ ሒዱ ብዬ የማዝበት ሥልጣኑ የለኝም፤ ነው የእኔ አቋም፡፡ የቅዱስነታቸውም ቤተሰቦች፣ ጎንደርም፣ ባሕር ዳርም፣ ደብረ ታቦርም ቀድመን መርሐ ግብር ይዘናል፤ ፕሮግራም ከተያዘ በኋላ መሰረዝ ሕዝብ ጋራ መጣላት ነው፤ አሉ፤ ይህን ሲሉ ጊዜ እኔም፣ እንግዲያው ካልተስማማችሁ ምንም ማድረግ አልችልም ብዬ በጠየቁት መሠረት ፈጽሜያለሁ፡፡

ቤተ ሰዎቻቸው የሚባሉት፥ በሥጋ ዝምድና ወንድማቸው ገብረ መስቀል የተባሉ አሉ፤ ፕሮቶኮል ይኹኑልኝ ብለው በአካባቢው የሕግ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት አሉ፤ ቅዱስነታቸው ራሳቸው ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በጠየቁት መሠረት እርሳቸውን መድበናል፤ ነርስ ደግሞ ከምግባረ ሠናይ ጠቅላላ ሆስፒታል በደብዳቤ ጠይቀን አንዲት እማሆይ መድበናል፤ እንዲያውም ትርፍ ሰዓት የምሠራበት አበል ይጨመርልኝ፤ መሣሪያዎች ይሟሉልኝ ብለው ጠይቀው አጽድቀናል፤ አቡነ ቀሲስ እና ቁልፍ ያዥ የኾኑ ኹለት መነኰሳትን በምርጫቸው አቅርበውልን መድበልናቸዋል፤ ልዩ ረዳቶቻቸው ናቸው፤ ራሳቸው ያመጡትን ሹፌር ቀጥረናል፤ አመቺ ተሽከርካሪ እስኪገዛ ድረስ ለጊዜው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጊዜ ከተገዙትና ቅዱሳን ፓትርያርኮች ከሚገለገሉበት መኪና አንዱን መድበናል፤ ወጥ ቤት ቤተ ሰዎቻቸው ያመጡትን ቀጥረናል፤ ከመጡበት ከነሐሴ ወር ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሚያገኙትን ያህል የወር ደመወዝ፣ አበል፣ የምግብ ወጪ በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስወስነን መድበናል፡፡ አሁን ለገቡበት ማረፊያቸው የተሟላ የቤት ዕቃ ብዙ ብር አውጥተን አሟልተናል፤ ከዚህም በኋላ የሚያስፈልግ ነገር ቢኖር ጥያቄያችሁን በሥርዓት አቅርቡ፤ ለመመለስ ዝግጁ ነን፤ ብዬ በቀደም ዕለት ሰብስቤያቸው መመሪያ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡

ሌላ ማንም መግባት አይችልም፤ አደጋ ቢፈጠር ተጠያቂዎች ናቸው፤ መጀመሪያ ጎንደር እንሔዳለን ብለው ጽፈው የጠየቁት እነርሱ ናቸው፤ መጀመሪያ አኵስም እንዲሔዱ ጥያቄ መኖሩ ተነግሯቸዋል፤ እነርሱ ግን መጀመሪያ ጎንደር ነው የምንሔደው አሉ፤ ከሦስት ሳምንት በፊት ነው ወንድማቸው፣ ፕሮቶኮላቸው፣ እነአቡነ በርናባስ መጥተው የጠየቁኝና ለሦስቱ አህጉረ ስብከት(ሰሜን ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደቡብ ጎንደር) በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ደብዳቤ ተጽፎ የአየር ትኬቱ፣ አበሉና ትራንስፖርቱ የፈቀድኹላቸው፡፡ ረዳቶቻቸው ኹሉ አሉ፤ በመኪና ቀድመው የሚሔዱት በመኪና ሔደዋል፡፡ ተቋም ስለኾነ የሚጠየቀው ነገር ኹሉ በጽሑፍ ነው መቅረብ ያለበት፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም ወደ አንድ ቦታ ሲሔዱም እኮ ልዩ ጽ/ቤታቸው፣ በበላይ ሓላፊው ብፁዕ አቡነ ገሪማ ፊርማ ጠቅላይ ጽ/ቤቱን በደብዳቤ ጠይቆ ነው የአየር ትኬት፣ የውሎ አበል፣ ትራንስፖርት የሚመቻቸው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩን ወደዚህ ሒዱ ብለን ግን አናዝዝም፡፡ የአኵስሙን ጉዞ በተመለከተም፣ ሓላፊነት ወስዶ ደብዳቤ ጽፎ ያመጣልኝ ማንም የለም፤ ይኼ ቃሌ ነው፤ ይመዝገብልኝ፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.