ለብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ፤ “እንኩቶ” ብለው የናቁት “አሻሮ” እንዳያደርግዎት!

Source: https://ethiothinkthank.com/2020/03/29/general-tefera-mamo/

በብዙ ሰዎች ውትወታ ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ አውሎ ሚዲያ ለተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል የሰጡትን አስተያየት ተመለከትኩት። ውይይቱ በሁለት አጫጭር ክፍሎች የቀረበ ሲሆን ሁለቱንም ክፍሎች ደጋግሜ አየሁት። አንድን ቃለምልልስ ደጋግሞ የመመልከት ልማድ ባይኖረኝም ያለወትሮዬ ይሄን ቃለምልልስ ደጋግሜ ተመለከትኩት።

በመጀመሪያ ደረጃ አውሎ የተሰኘው ቻናል በወያኔዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ነው። ሁለተኛ ቃለምልልሱን ያደረገው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ከያየሰው ጋራ አፍና ጭንቅለቱን ለወያኔ አሳልፎ የሸጠ አገልጋይ ነው። በመሆኑም ሚዲያውም ሆነ ጋዜጠኛው በአማራ ክልል አመራሮች መካከል ያለው ክፍተት ይበልጥ ለማስፋት ጥረት ማድረጋቸው ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነገር ነው። በመሆኑም የብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ ቃለምልልስ በአማራ ልሂቃን መካከል አለመግባባትና ግጭት ለመፍጠር ያለመ ነው።

በእርግጥ ከ15ቱ ግድያ በኋላ መታሰራቸው፣ ከእስር ከወጡም በኋላ በክልሉ መንግስት በተሰጣቸው የሥራ ቦታ ደስተኛ አለመሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል። ሆኖም ግን በውስጣቸው የታመቀውን አጉል እልህና ስሜታዊነት ለመግለፅ የወያኔዎች ሚዲያ ጋር መሄዳቸው ያስገምታቸዋል። በቃለምልልሱ የተናገሩትን በጥሞና ላጤነ ደግሞ ጄኔራሉ በራሳቸው ላይ ሌላ ጣጣና መዘዝ እንዳያመጡ ያሰጋል።

ከመጀመሪሪው ጀምሮ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ፣ ብ/ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና የብ/ጄ ከማል ከልቹ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የፀጥታ ቢሮ ውስጥ በሃላፊነት ሲሾሙ ተቃውሜያለሁ። ምክንያቱም ለጦርነት የሰለጠኑ ሰዎች የፖለቲካ ኃላፊነት መስጠት ፈፅሞ ትክክል አይደለም። የጦር ጄኔራል የክልል ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ሲሾም የክልሉ ነዋሪ በሙሉ ወታደር ይመስለዋል። ሁሉም የፀጥታ ችግር በወታደራዊ ጉልበት ለመፍታት ጥረት ያደርጋል። ይህ ደግሞ በተለይ በአማራ ክልል ምን እንዳስከተለ በተግባር አይተናል።

ብ/ጄኔራል ተፈራ ካለፈው ስህተት የተማሩ አይመስለኝም። ከዚያ ይልቅ የቀድሞ ቦታቸው ላይ ባለመመለሳቸው ከፍተኛ እልህና ቁጭት ውስጥ የገቡ ይመስላል። በተጠቀሰው ቃለምልልስ ላይ የተናገሩት ነገር ይህን አሉታዊ ስሜት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ለምሳሌ በስሜት ውስጥ ሆነው የሰኔ 15ቱን ግድያ ተከትሎ የክልሉ ልዩ ኃይል በመከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህ ላይ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በጃዊ ወረዳ፣ ቅማንት እና ከሚሴ አከባቢዎች በተፈጠረው ግጭትና የሰዎች ግድያ የነበራቸውን ሚና ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው ጄኔራሉ ራሳቸውን በራሳቸው ጠልፈው ለመጣል ቁልቁል እየተንደረደሩ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። ጄኔራል አሳምነው ፅጌን እስከዛ ድረስ ያደረሰው በተጠቀሱት ሦስት ቦታዎች ላይ በክልሉ ልዩ ሃይል የተፈፀሙትን የወንጀል ተግባራት የሚያጣራ የመርማሪ ቡድን መላኩ እንደሆነ ይታወሳል። ይህ መርማሪ ቡድኑ በጃዊ፣ ቅማንትና ከሚሴ አከባቢዎች በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳትና ጥፋት ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ በግልፅ የሚያሳይ የምርመራ መዝገብ ተጠናቅሮ አስቀምጧል። ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ ደግሞ ከባልንጀራቸው ጋር የሚያወጉ ይመስል “የክልሉ ልዩ ሃይል እርምጃ እንዲወስድባቸው አደረግን….” ቅብርጥስ እያሉ በራሳቸው ላይ ይመሰክራሉ።

በመጨረሻም ብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከወያኔዎች ሚዲያና አገልጋይ ፊት ቁጭ ብለው በተናገሩት ነገር የወያኔ መጠቀሚያ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ በተጨማሪ ከንግግራቸው እንደተረዳሁት በቀጣዩ የወያኔ የጥፋት እቅድ ትግበራ ሂደት ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ካሉት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አላስፈላጊ ፀብና ግጭት ውስጥ መግባታቸው፣ በዚህም የስራ ባልደረቦቻቸውን በሚያሳፍር መልኩ በይፋ መሳደብና ማንጓጠጥ መጀመራቸው ሳያንስ፣ በእልህ ተገፋፍተው የወያኔዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ በጣም እሰጋለሁ። “የጤፍ ያህል የሚበልጥህ ሰው ጤፍ ሊያሳክልህ ይችላል” እንደሚባለው ሁሉ “እንኩቶ” እያሉ ያጣጣሏቸው ባለስልጣናት ግዜና ቦታ ጠብቀው “አሻሮ” ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ማወቅ አይከፋም።

Share this post

One thought on “ለብ/ጄኔራል ተፈራ ማሞ፤ “እንኩቶ” ብለው የናቁት “አሻሮ” እንዳያደርግዎት!

  1. Dear commentator, it is clear where you are standing! Your comment represents the Sene 15 killers and the events before that the armed forces of OLF(including the ruling group) and TPLF raid and killings of the Amahara people within its region. Had your comment had substance, how do you think a military general is assigned in civilian institution like water resources management adviser? this is the usual conspiracy politics and don’t worry your comment represents the usual illogical suppression of the Amhara people which will lead the nation not to prosperity.

    Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.