ለአሸንዳ ሴት የሚሰጠው ክብር ለሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች በ365ቱ ቀናት ሊሰጥ የሚገባ ነው-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

Source: https://fanabc.com/2019/08/%E1%88%88%E1%8A%A0%E1%88%B8%E1%8A%95%E1%8B%B3-%E1%88%B4%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%88%B0%E1%8C%A0%E1%8B%8D-%E1%8A%AD%E1%89%A5%E1%88%AD-%E1%88%88%E1%88%81%E1%88%89%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8A%A2/

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለአሸንዳ ሴት በዓሉ በሚከበርበት ቀናት የሚሰጠው ክብር ለሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች በ365ቱም ቀናት ሊሰጥ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የአሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል ደረጃ “አሸንዳ የሰላም፣ አንድነትና ልማት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል በዛሬው እለት በመቐለ ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ በርካታ የፌደራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ዘንድሮ “አሸንዳ የሰላም፣ አንድነትና ልማት ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው የአሸንዳ በዓል ላይ መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አሸንዳ ያሉ የበርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ነች፤ እነዚህ ሀብቶች ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም ተንከለባክበንና ጠብቀናቸው ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ከቻልን አሁን ካለው በላይ አኩሪ እና ጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያስገነዘቡት።

የአሸንዳ በዓልን በቀጣይ ልክ እንደ መስቀል፣ ፊቼ ጨምበላላ እና የገዳ ስርዓት ሁላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት እንደሚመዘገብ እምነት አለኝ ብለዋል።

በዓሉ ለዚህ እንዲደርስ ያደረገው የትግራይ ህዝብ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል።

“ባህልን የፖለቲካ ድንበር አይገድበውም” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወረቅ፤ የአሸንዳ በዓልን ዓለም እንዲያውቀው ለማድረግ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠብቅም አሳስበዋል።

በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን የሀገሪቱ ባህሎች እንዳይበረዙ እና ከምንጫቸው እንዳይጠፉ የመጠበቅ እና የመንከባከብ ሀላፊነት የሁሉም አንደሆነም አስገነዝበዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አልከውም፥ የአሸንዳ በዓል በሚከበርበት ወቅት ለአሸንዳ ልጅ ልዩ ክብር እንደሚሰጥ በመጥቀስ፤ ለአሸንዳ ልጅ የሚሰጠው ክብር በበዓላቱ ቀናት ብቻ ሳይሆን በ365ቁ ቀናት ለሁሉም የኢትዮጵያ ሴቶች ሊሰጥ እንደሚገባም ገልፀዋል።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ለሴቶች በርካታ አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም በመግለጽ፤ በቀጣይም ያለእድሜ ጋብቻን እና ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በቅጡ መከላከል አለብን ብለዋል።

የአሸንዳ በዓልን ተባብረን እንዳከበርን ሁሉ ሀገራችንንም ተባብረን ልንጠብቅ ይገባል ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መልእክት አስተላልፈዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ “የአሸንዳ በዓል ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላችን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ደብረጺዮን ባስተላለፉት መልእክት፥ “የአሸንዳ ልጆች በዓላችሁን እና ክብራችሁን ለመግለጽ እንዲሁም ለዓለም ለማስተዋወቅ በማለም በባህላዊ ልብሶች ተውባችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።

“ትግራይ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባህሎች እና ቅርሶች መገኛ ናት” ያሉት ዶክተር ደብረጺዮን፥ የትግራይ ህዝበም ቢሆን ባህሉን እና ማንነቱን ለረጅም ዓመታት ተንከባክቦ ያቆየ ህዝብ መሆኑን ገልፀዋል።

የአሸንዳ በዓል በቱሪዝም መስህብነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ የሀይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫውን ጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ሰው ግዴታውን መወጣት አንዳለበትም መልእክት አስተላልፈዋል።

በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ነው ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ያስታወቁት።

ዶክተር ደብረጺዮን፥ የአሸንዳ ልጆች የሰላም እና የፍቅር መገለጫ በመሆን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ስለ ፍትህ፣ ሰላም እና ልማት መረጋገጥ አንድነታቸውን ጠብቀው መቀጠል አንዳለባቸወም አስገንዝበዋል።

በትግራይ እየታዩ ያሉ የሴቶች ጥቃት በንግግራቸው የኮነኑት ዶክተር ደብረጺዮን፥ ይህንን በመከላከል ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

በደስታ ተካ እና በሙለታ መንገሻ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.