ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጥ!!

Source: http://moreshinfo.com/archives/3692

ዶ/ር አብይ አህመድ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ተመርጠው የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ከሚያዚያ ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ጀምሮ ይሄውና ሰባት ወራት ሊሆናቸው ነው። እርግጥ ነው በነዚህ ሰባት ወራቶች ውስጥ መልካም የለውጥ ጅምሮች መኖራቸው አሌ የሚባል አይደለም። በተለይም ደግሞ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም ጅማሮና በትግሬ ወያኔ በግፍ እንደ ወፍ ተባረው በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ/እንድናደርግ በሩን መክፈታቸው እጅግ በጣም የሚያስመሰግናቸው ከመሆኑ በላይ በየእስር ቤቶች ግፍ ይፈጸምባቸው የነበሩ ወገኖቻችን (ሁሉም ባይሆኑም እንኳ) እንዲፈቱ ያደረጉት ጥረትና እርምጃ በሁሉም ልቦና ምስጋና ተችሮታል።
ይህን የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ለተወዳዳሪ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ያቀረቡትን ብሔራዊ ጥሪ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም(ዐኅኢአድ) እንደሌሎች ሁሉ ጥሪውን በደስታ ተቀብሎ ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ
መንገድ ግድያ፣ ግፍና መከራ ለ፳፯ ዓመታት ከሚፈራረቅበት ሕዝባችን ጋር ፊት ለፊት ከመወያየት አልፈን ቀደም ብሎ ዐኅኢአድ በሕቡ ጀምሮአቸው የነበሩትን ድርጅታዊ እንቅስቃዎች በግልጽና ሰፋ ባለ መልኩ ድርጅታዊ መዋቅሮችን
እየዘረጋን እንገኛለን። ይህ መልካም የለውጥ ሁኔታ የተገኘው ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድና የስራ ባልደረቦቻቸው በወሰዱት ቆራጥ ሀገራዊ እርምጃ ነውና ዛሬም ምስጋናችን በድጋሜ ከፍተኛ ነው።  እርግጥ ነው በየአደባባዩ በአጋዚ ቅልብ ጦር ጥይት በግፍ የተረፈረፉትና በጌታቸው አሰፋ (ምድረሲኦል) መስሪያ ቤት በየእስር ቤት ለሞትና ለእንግልት ተዳርጎ ይማቅቅ የነበረው ትውልድ ጥያቄው አንድና አንድ ነው። ያም ጥገናዊ ለውጣ ሳይሆን “መሰረታዊና…መሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ” መሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም።
ይሁን እንጅ ይህ የሕዝባችንን መሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ጭራሽ ጊዜ የማይሰጣቸው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ከፊታችን ላይ ስለተደቀኑ የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ እንዲጎለብትና ስር እንዲሰድ ከተፈለገ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይና የቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ክፍተኛ ትኩረት ሰጠው አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ ዐኅኢአድ በአንክሮ አሁንም በድጋሜ ይጠይቃል። እነሱም፦

፩ኛ/ የትግሬ ወያኔ የ፳፯ ዓመታት መድⶀአዊና ፋሽስታዊ አገዛዝ መገለጫው (በዋና መልኩ) በዐማራ ነገድ ላይ እየተፈጸመ ባለው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ መሬትና ሀብት ነጠቃ ነውና ይህ አሳሳቢ ጉዳይ አሁንም ከ፲፻፸፪ ዓ.ም ጀምሮ በትግሬ ወያኔ በኃይል በወረራ በያዛቸው የዐማራ ግዛቶች በሆኑት በወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ እንዳ መሓሪ፣ በራያ አዘቦ፣ ወፍላና አላማጣ ዛሬም ድረስ (እንዲሁም በሂደት በመተከል ጭምር) በወገኖቻችን ላይ ግድያ፣ አፈናና ማፈናቀል ተባብሶ የቀጠለ በመሆኑ ይህ ዐይን ያወጣ ሕገወጥ ድርጊት ያለምንም ቅድመሁኔታ እንዲቆም ዐኅኢአድ በድጋሜ ይጠይቃል። እንደ ጊዜአዊ መፍትሔ ሃሳብም አካባቢው ከትግሬ ወያኔ ስውር ታጣቂና ልዩ ኃይል ነፃ ሆኖ ሁነኛ የመፍትሔ ሃሳብ በአግባቡ እስኪሰጥ ጊዜ ድረስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በነዚህ ቦታዎች እንዲሰፍር፣ ጸጽታውን እንዲቆጣጠርና ወገኖቻችንን ከግድያ እንዲታደግ በአንክሮ ዐኅኢአድ ይጠይቃል።

፪ኛ/ ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ ምንም እንኳን ሀገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ነች ቢባልም እንኳ አሁን በተለያዩ ቦታዎች የሚታዩት ሕገወጥ ድርጊቶች (ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ግጭቶች፣ ወዘተ) ወደ አላስፈላጊ
መሰሳቦችና የከፉ ችግሮች እንዳያመሩና የተጀመረውን ለውጥም ቀጣይ ለማድረግ እንዲያስችል እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሕግንና ሕግን መሰረት አድርጎ በሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል መርህ ላይ መመርኮዝን ሁኔታው የግድ ይላል።
እናም በዚህ ረገድ ከዚህ መርህ አፈንግጠው የወጡ እንቅስቃሴዎችና ዛቻዎች በተሎ እልባት ሊደረግባቸው ይገባልና መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
   በተለይም ደግሞ አንዳንድ ቡድኖችና ግለሰቦች ራሱን የቻለ “ሁለተኛ መንግሥት የሚመሩ” እስከሚመስሉ ድረስ እርቆ በመሄድ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ለማንም የማይበጅ መሆኑ ታውቆ እንደዚህ ካለ ግብዝና ትዒቢታዊ አነጋገርና እወጃ
እንዲታቀቡ ተገቢው ሕጋዊ ምክርና ተግሳጽ ሊሰጣቸው ይገባል። እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ቢኖር አሁን ለተፈጠረው መልካም ሁኔታም ቢሆን ላለፉት ፳፯ ዓመታት የትግሬ ወያኔ/ኢሕአዴግ በሕዝባችን ላይ በፈጸመው ግድያና ባሳረፈው የጭካኔ ብትር የተማረረው ወገናችን ከአጋዚ ቅልብ ጦር ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ በከፈለው ከባድ የሕይወት መሰዋዕትነት የተገኘ ድል እንጅ በሩቅ በሰማ በለው ባደረጉት ከፋፋይ ቅስቀሳ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባ ነበር።
እናም አሁን እየሰማነው ያለው ግብዝ አነጋገርና ሕገወጥ ወታደራዊ ድርጊታቸውን መንግሥት እንደ መንግስት ኃላፊነቱን በመገንዘብ ሥርዓት ሊያሲዛቸው ይገባል። ይህ መቼም ቢሆን እጅግ በጣም አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነውና መንግስት በመላ ሀገራችን መረጋጋት እንዲፈጠር የራሱን ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ሕጋዊ ሲባልም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ወጣቶች ላይ የተወሰደው ዓይነት ፍረደ ገምድልና አሳዛኝ አሮጌ የትግሬ ወያኔ ድርጊት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
በዚህ አጋጣሚ ለሦስተኛ ጊዜ በአጽነዖት የምንጠይቀው በአዲስ አበባ ሰላማዊ ወጣቶች ላይ ፖሊስ የወሰደው የአፈሳ እርምጃ መላው ሕዝባችንን እጅግ በጣም ያሳዘነን መሆኑን እየገለጽን ከሕግና ሕጋዊነት አኳያም ድርጊቱ ሕገወጥና እጅግ
በጣም የማይታመንና አስደንጋጭ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ወጣቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ለሦስተኛ ጊዜ እንጠይቃለን!! ሌላው ግን መቸም ቢሆን የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የሰላምና የመደመር ጥሩ አባባልን ለዐማራ ወገናችንና በዐማራ ነገድ ዙሪያ ለተደራጁ ድርጅቶች በደስታ የምንቀበለውና የምንደግፈው ለመሆኑ ጥያቄ አይነሳም። ምክንያቱም አብሮነት፣ መቻቻል፣ ሰላምና አንድነት፣ ፍትሕና ርዕትህ ለዐማራ ነገድ ተወላጆች ተፈጽሮአዊ ባሕሎቻችን መሆናቸው ለማንም ግልጽ ሊሆንለት ይገባል።  ለዚህ ደግሞ በሰኔ ፲፮ትና ከዚያም በኋላ በየአደባባዩ ግልብጥ ብሎና መንገዱን አጨናንቆ ለድጋፍ ሰለፍ የወጣው (በዋና መልኩ) ዐማራው ለመሆኑ ዛሬም ቢሆን ቋሚ መስክር ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ምን እንድሆንም በሚገባ ስለሚታወቅ በድጋሜ ማንሳት አያስፈልግም።

ይሁን እንጅ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ጥቅምት ፮ ይፋ የሆነው የካቢኔ አሿሿም አፍ አውጥቶ እየተናገረ ያለው ብአዴን/አዴፓ ለኦዴፓ በስትራቴጅ የትግል አጋርነት ሆኖ ተደጋግፎ የመሄድ አካሄድ ሳይሆን የታየው ለጊዜአዊ ማናጆና መረማመጃ መሆኑ ግልጽ መሆኑ ነው። ይህ መቸውንም ቢሆን አስገራሚና ከፍተኛ ክሕደት ይመስላል።  ድርጊቱን አሳዛኝ ያደረገው ደግሞ የብአዴን/አዴፓ አሁንም እንደ ለመደው ማናጆ ሆኖ መቆጠሩ ብቻ ሳይሆን ዐማራው ባለው የሕዝብ ቁጥር ብዛት እንኳ ተገቢው ቦታ ሊሰጠው ሲገባ ይህም ሊሆን አለምቻሉ ነው። እንዲያውም ሕሊና ላለው ዐማራ በትግራ ወያኔ ይዘወር በነበረው የኢሕአዴግ መንግስት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ከፖለቲካውና ከኤኮኖሚው ተገሎ የመኖሩን ያህልና ሕዝባችን ለለውጡ የከፈለውን ከባድ የሕይወት መስዋዕትነትን ግምት ውስጥ በማስገባት በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ መንግስት ተገቢው ቦታ ሊሰጠው ሲገባ አሁንም በዚያው በተለመደው የማግለል ፖለቲካ እየተገፋበት ያለ መሆኑ ያሳዝናል።  በጣም የሚገርመው ደግሞ ሁሌም ለዐማራው የተመደበችው ያችው ጠማማው ሚኒስቴር (ት/ሚ)ተብሎ የሚታወቀው ትምህርት ሚኒስቴር መሆኗ ነው። ያም ቢሆን ተቀንሶላት!! በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም ለዚህ ሁሉ ማጣጣልና ስላቅ የዳረገን የዐማራው በነገዱ ዙሪያ ጠንክሮ ከመታገል ይልቅ ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን ኢትዮጵያ እያለ ሲሸውዱት ለኖሩትሲያቀብል የኖረ በመሆኑ እጁ አመድ አፋሽ በመሆኑ ነውና ከዚህ በላይ ብዙ ማለት አያስፈልግም። በሌላ በኩል ደግሞ በመጨረሻ ሰዓትም እንኳ ቢሆን ዐማራ ለኅልውናው ሲል በነገዱ ዙሪያ መደራጀቱን እንደ ወንጀል በመቁጠር በየመድረኩ ሲያብጠለጥሉትና አቆሽሾ በማቅረብ ዛሬም በዐማራው ላይ ሌላ ዙር የሥነልቦና ጦርነት በስፋት ተከፍቷል።  ነገሩ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዲሉ እነዚህ ኃይሎች ሲፈልጉም “በዐማራነት መደራጅት የትግሬ ወያኔን መንገድ መከተል ነው” ብለው አሁንም ዐማራውን ሊያሞኙትና ሊያፈዙት ብዙ ሲጥሩ እየታየ ነው። ዐማራው ጠ/ሚ ዶ/ር አብይን ደግፎ በግልጽ የቆመበት ዋናው ሚስጢር “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ባሉት ንግግር መሆኑ እየታወቀ ዐማራውን ኢትዮጵያዊነት ሊያስተምሩት መመከራቸው እጅግ በጣም አስገራሚ ነው። በሌላ አገላለጽ ዐማራው ላለፉት ፴ ዓመታት ለዘር ፍጅት እየተዳረገ ያለው ኢትዮጵያን ከልቡ ይወዳል በሚል እሳቤ ተሂዶ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ ዐማራው ራሱን ከዘር ፍጅት ለመታደግ እያደረገ ያለውን የኅልውና ትግል በየአደባባዩ ማጣጣልና ማራከስ አሁንም ለዐማራ ጠላቶች ቀጥተኛ ተባባሪ ከመሆን ተልይቶ አይታይም። ድርጊታቸውን እንቆቅልሽ ያደረገው ደግሞ ዐማራው በሚሰጣቸው ሰፊ ገንዘብ ትላንት አክራሪ ብሔርተኛ ድርጅቶችን በየአደባባዩ ሲያጠናክሩ እንዳልነበር ሁሉ የዐማራ በነገዱ ዙሪያ መደራጀት ለምን እንደሚከነክናቸው ይገርማል!! ለዚህም ነው ከላይ “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” የምንለው። ምክንያቱም ዐማራ በነገዱ ለመደራጀት የተገደደበት ዋናው ምክንያት በዐማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት መነሻ መሰረቱ “ሕገመንግስታዊ በመሆኑ ነውና”። እናም ዐማራውን በነገዱ ዙሪያ አትደራጅ ብሎ በየአደባባዩ ከማውገዝ ይልቅ ለዐማራ መደራጀት ምክንያት የሆነውን ሕገወጡን የትግሬ ወያኔና ኦነግ ሕገመንግስትና ክልል ተብዮውን አምርረው ሊያወግዙት ይገባ ነበር!!

የትግሬ ወያኔና ኦነግ ሕገወጥ ሕገመንግስት በሕዝብ ቀጠተኛ ተሳትፎ ወደ ኢትዮጵያዊነት ሕገመንግሥት ሲለወጥ ያን ጊዜ ዐማራው በነገዱ ዙሪያ መደራጀቱን አቁሞ “በዜግነት ፖለቲካ” ላይ ከሚሰሩ አቻ ድርጅቶች ጋር ሆኖ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በጋራ ይሰራል።  ይህ ደግሞ የዐኅኢአድ ድርጅታዊ ግብ መሆኑን አሳምረው ያውቁታል። በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የዐማራን መደራጀት በየአደባባዩ የሚያወግዘው አካላት “ስለ ዜግነት ፖለቲካ” ቢያወራም የትግሬ ወያኔና ኦነግን የጋራ ሕገወጥ ሕገመንግስት ግን ጭራሽ አይነኳትም። በተለይ ደግሞ የዚሁ ሕገመንግስት የመሬት ነጠቃ መገለጫ የሆነውን “ክልል” ስለሚባለው ለይስሙላ እንኳን ሊያወግዝው ይቅርና የፌዴራል መሰረቱ የማዕዘን ድንጋይ አድርጎ እየቀሰቀሰበት ያለ መሆኑ ነዉ።  ለዚህም ነው “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ስንልም “ሕገወጡን ሕገመንግስት ከማውገዝ ይልቅ ዐማራው ለኅልውናው ሲል እያደረገ ያለውን መደራጀት ማውገዝ ይቀላቸዋል የምንለው”።  ከላይ በተራ ቁጥር ፩ ና ፪ ለተነሱት አሳሳቢ ጉዳዮች መንግስት በአስቸኳይ እልባት ከመፈለግ ባሻገር ለውጡንም  ባስተማማኝ ሁኔታ ቀጣይ ለማድረግ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድና ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን የኢሕአዴግ የአዋሳ ጉባኤ ሕጋዊ ተመራጮጭ የመሆናቸውን መልካም አጋጣሚና ውክልና ግምት ውስጥ በማስገባት በቀሪ የመንግስት ከፍተኛ መዋቅሮች ላይ የተፈጠረውን ክፍተት የሚያካክስ አመዳደብ ሊከተሉ ይገባል የሚል እምነት ዐኅኢአድ አለው። ይህም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን በቀጥታ በማሳተፍ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ጅማሮ እንዲመጡ ዐኅኢአድ ይጠይቃል።
በተለይም ደግሞ ላለፉት ፳፯ ዓመታት በትግሬ ወያኔ የፊጥኝ ታስረውና ተወረው ያሉ መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት ጭምር ለምሳሌ ያህል፦ ኢትዮጵያ አየር መንግድ፣ ባንክ፣ ፋይናስ፣ ፖሊስ፣ የደኅንነት፣ ወዘተ ኃላፊነት
በሚሰማቸው አዳዲስ ተሿሚዎች እንዲተኩ በድጋሜ እናሳስባለን።

አንድ በግልጽ ያየነውና አስቀድመን የገመትነው ደካማውና አቅመቢሱ ትምህርት ሚኒስቴር አሁንም ያው ለዐማራ ተብዮዎች የተሰጠ መሆኑን አሰልች ዜና ከመሆኑ ባሻገር ዳግማዊትን ከአዲስ አበባ ከንቲባናት ለማራቅ ሲባል የተወሰደው እርምጃ  ይበልጥ ጥርጣሬ ውስጥ እንድንወድቅ አድርጎናል። አዲስ አበባ በነዋሪዎች ትመራ የሚለው ጠንካራ መፈክር ሲነሳ ነዋሪው ዐይኑን የጣለ በዳግማዊት ላይ መሆኑ በግልጽ ይታወቅ ስለነበር ዳግማዊት ወደ ሌላ ቦታ ባትሄድ የተሻለ ይሆን ነበር።

በመጨረሻም ዞሮ ዞሮ መዝጊያ ጭራሮ እንደሚባለው ሁሉ እስካሁን ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድና ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን የሄዱበት የለውጥ ሂደት መልካም ነው ቢባልም እንኳ ሕዝባችን የሚፈልግውን የሥርዓት ልውጥ ሕውን ለማድረግ ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ከተወዳዳሪ ድርጅቶች ጋር በጋራ መድረኮች ላይ ቁጭ ብሎ በሀገራችን መጻአዊ ዕድል ፋንታ ላይ መወያየት ተገቢ መሆኑን ትኩረት እንዲሰጠው ዐኅኢአድ በአንክሮ ይጠይቃል። ምንም እንኳን በታሪክ አጋጣሚ ኢሕአዴግ መንግስት እየመራ ያለ ነው ቢባልም ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ከተወዳዳሪ ድርጅቶች ጋር መወያየት አለበት። ስርቼ አቀርባለሁ፣ አሸጋግራለሁ የሚለውን ለመቀበል በጣም ከባድ ነውና ሕዝባችን የሚፈልገውን የሰላምና ዴሞክራሲ ዋስትና እንዲኖረው ግልጽ የጋራ ውይይት የግድ ሊጀመር ይገባል። ውይይቱ ለሀገር ውስጡ ብቻም ሳይሆን በየአህጉሩ እየተደረጉ ያለው ግንኙነት ሳይቀር ግልጽ ሆኖ ለሕዝባችን ሊቀርብለት ይገባል። እኛም እንደ ድርጅት ልናውቀውና የድርጅታችንን አቋም ለሕዝባችን ልንገልጽ ይገባል።

የዐማራ ኅልዉና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነዉ!!

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.