ለአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎች የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ የጂፒኤስ ሥርዓት ተገጥሞላቸው ወደ ስራ ሊገቡ ነው ተባለ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/132883

የታገዱት የአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎች የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ የጂፒኤስ ሥርዓት ተገጥሞላቸው ወደ ስራ ሊገቡ ነው ተባለ
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የታገዱት የአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎች የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ የጂፒኤስ ሥርዓት ተገጥሞላቸው ወደ ስራ ሊገቡ ነው ።
በከተማዋ ውስጥ ሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለውን እገዳን በተመለከተም የተጠየቁት ም/ከንቲባው እዚህ ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት በየአንዳንዱ ቀን አዲስ አበባ ውስጥ በሞተር ሳይክሎች አማካይነት ዝርፊያ ይፈጸም ነበር ብለው፤ በዚህ ምክንያትም ሞተር ሳይክሎች ላይ በተጠና መልኩ ክልከላ መጣሉን ይናገራሉ።
እስካሁን የነበረው ሁኔታ ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡትን ሞተር ሳይክሎች ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ነገሮች እንዳልነበሩና በዚህም ምክንያት ዝርፊያና የደህንነት ስጋት እንደተፈጠረ በመግለጽ “በቀጣይ ሞተር ሳይክሎቹ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ሕግና ደንብ ይዘጋጃል” ብለዋል።
የከተማው አስተዳደር ሞተር ሳይክሎች ላይ እገዳውን ከጣለበት ዕለት ጀምሮ “በሚያስደንቅ ሁኔታ በከተማዋ ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። ያጋጥሙ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ከግማሽ በላይ በሆነ ሁኔታ ለመቀነስ አስችሏል” ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።
ስለሞተር ሳይክሎቹ ዝርዝር መረጃ እንኳን እንደሌለ እገዳውም ያሉት ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ እንደሚቆይ የሚናገሩት ምክትል ከንቲባው አስፈላጊው ህጋዊ የቁጥጥር ሥርዓት ከተዘረጋ በኋላ ግን ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ገልጸዋል።
ም/ከንቲባው አክለውም ሞተር ሳይክሎቹን የመቆጣጠሪያ ዘመናዊ የጂፒኤስ ሥርዓት እንደሚዘረጋ አመልክተው፤ ከሚዘረጋው ሥርዓትና ደንብ ውጪ ማንም በከተማዋ ውስጥ እንዲሰራ አይፈቀድለትም ብለዋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.