ለኢትዮ ሶማሌ ተጎጅዎች ተከታታይ የገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፤ የበረከት መታሰቢያ ካርዶች በስርጭት ላይ ናቸው

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2018/08/20/%E1%88%88%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE-%E1%88%B6%E1%88%9B%E1%88%8C-%E1%89%B0%E1%8C%8E%E1%8C%85%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8A%A8%E1%89%B3%E1%89%B3%E1%8B%AD-%E1%8B%A8%E1%8C%88%E1%89%A2-%E1%88%9B/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2018/08/jigjiga-bereket-masetawosha.jpg

FB_IMG_1534692602768

  • ከመጀመሪያው እንቅስቃሴ፣ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ በተስፋ ሰነድ ተገኘ፤
  • ከ50 እስከ 500 ብር ያሉ 80ሺ የመታሰቢያ ካርዶች በስርጭት ላይ ናቸው፤
  • አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ የካርዶቹን ሥርጭትና ሽያጭ ያስተባብራሉ፤
  • በሙሉ ለሽያጭ ሲውሉ፣ 11ሚ. ብር ያህል ገቢ እንደሚያስገኙ ተጠቆመ፤
  • የአልባሳት ርዳታውን፣በየአጥቢያው የማሰባሰቡ ሒደት ተጠናክሮ ቀጥሏል፤
  • በአካልም ተገኝቶ ተጎጅዎችን ማበርታት እንደሚያስፈልግ ሊቀ ጳጳሱ አሳሰቡ
  • ክልሉም፣የፈረሱትን አብያተ ክርስቲያን በበጀቱ የማሠራት ሓላፊነት አለበት፤

/መ/ር ብርሃኑ አድማስ/

†††

በኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት በተፈጸመው አሠቃቂ ግድያና ውድመት የተጎዱ ካህናትን፣ ምእመናንንና አብያተ ክርስቲያንን በዘላቂነት ለማቋቋም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተሠየመው ዐቢይ ኮሚቴ ሥር የሚንቀሳቀሰው የቅስቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ፣ ከመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብሩ ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ በተስፋ ሰነድ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

gebi asabasabi ena keskesa

ኮሚቴው፣ ትላንት እሑድ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሔደው የገቢ ማስገኛ መርሐ ግብር፣ ከ250 ያላነሱ ለጋሾች የተገኙ ሲኾን፣ በተሠራጨው የተስፋ ሰነድ(promissory note) ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለመለገስ ቃል እንደገቡ ገልጿል፡፡ ከጥሬ ገንዘብ ባሻገር በቁሳቁስም ረገድ፣ ዳግም ለሚገነቡት አብያተ ክርስቲያን፥ ሙሉ የቆርቆሮ ክዳን፣ የውስጥና የውጭ ቀለሞች ለማቅረብ ቃል የገቡ ባለሀብቶች መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡

በጎ አድራጊዎቹ፣ ኮሚቴው ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ካለፈው ሳምንት ረቡዕ አንሥቶ ለአምስት ቀናት በስልክ ባስተላለፈላቸው ጥሪMmr Birhanu Admas የተገኙ ናቸው፡፡ “የሱባኤ ሳምንት በመኾኑና በክረምቱ ቤተሰባዊ ዕረፍት ወደ ውጭ የተጓዙ ባለሀብቶች ጥቂት ባለመኾናቸው ቁጥሩ የተጠበቀውን ያህል ባይኾንም፣ውጤቱ በጣም ተስፋ ሰጪ ነው፤” ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ መ/ር ብርሃኑ አድማስ፣ ከመጪው ዓመት መስከረም ወር መባቻ በኋላ ተከታታይ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ለማካሔድ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ “እንዲህ በጥድፊያ አይኾንም፤ መድገም አለብን፤” የሚሉ አስተያየቶች ከተሳታፊዎቹ ከራሳቸው መቅረቡ፣ እንቅስቃሴውን በስፋት ለማከናወን እንደሚግዝ ተናግረዋል፡፡

በቅስቀሳና የገቢ ማሰባሰቡ፥ ሰባክያነ ወንጌል፣ ዘማርያን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና ማኅበራት ታላቅ ሓላፊነት እንደተጣለባቸው የጠቀሱት መ/ር ብርሃኑ፤ በተጎጅዎች ስም የተሰበሰበ ገንዘብ በተከፈተው የንግድ ባንክ አካውንት መግባት እንዳለበትና ለለጋሾች ያመች ዘንድ በሌሎችም ስምንት ባንኮች ተጨማሪ አካውንቶች በዚህ ሳምንት ውስጥ ይከፈታሉ፤ ብለዋል፡፡ አዲሶቹ አካውንቶች፣የንግድ ባንኩ ሒሳብ በተከፈተበት በሦስት ብፁዓን አበው(የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ) ይከፈታሉ፤ በጣምራ ፊርማ ይንቀሳቀሳሉ፤ቁጥሮቹንም በዚሁ ሳምንት በይፋ እንደሚያስታውቁ የኮሚቴው ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡

FB_IMG_1534680987281

ዮድ አቢሲኒያ ስፖንሰር ባደረገው በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅንና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ አምስት ብፁዓን አባቶች ተገኝተዋል፤ ቤተ ክርስቲያን በእሳትና በስለት ብትፈተንም፣ በረድኤተ እግዚአብሔርና በልጆቿ የተባበረ ጥረት ተጠናክራ እንደምትወጣው የሚያስገነዝቡ የጽናትና የተስፋ መልእክቶችን አስተላልፈዋል፡፡ በቅዱስ ራጉኤል የጎልማሶች ማኅበር እና በኮሚቴው አባል ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ ይህንኑ አጉልተው የሚያሰሙ መዝሙራት ቀርበዋል፤ የ12 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልምም ታይቷል፡፡

Yod Abyssiniaከትላንት በስቲያ ቅዳሜ፣ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጋራ በመኾን እዚያው ጅግጅጋ ሔደው ካህናቱንና ምእመናኑን ሲያጽናኑ ውለው የተመለሱ ሦስት አባቶች፣ መላው ኦርቶዶክሳውያን መርዳትና መተባበር እንዳለባቸው በአጽንዖት በማሳሰብ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከልኡካኑ አንዱ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እንደውም፣ የገንዘብና ንብረት ርዳታ ብቻ በቂ እንዳልኾነና በተጎጂ ወገኖቻችን መካከል ተገኝቶ ኹኔታውን መመልከት፣ ሠቆቃቸውን መካፈል እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

“ሥነ ልቡናቸውን መገንባት አለብን፤ የሰውም ረኀብ አለባቸው፤ ሰዉ በአካል ሒዶ መጎብኘት አለበት፤ ወንድም፣ እኅት አለን ብለው እንዲሰማቸው ጉዞ መደረግ አለበት፤ ገንዘቡ ብቻ በቂ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ እያሉ ነው፤ መሔድ አለበት ክርስቲያኑ፤ አብሮ በልቶ ጠጥቶ መምጣት አለበት ከእነርሱ ጋራ፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

በዚሁ የብፁዕነታቸው መልእክት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኮሚቴው ሰብሳቢ መ/ር ብርሃኑ አድማስ፣ “የደርሶ መልስ በረራ ጉዞ አቀናጁልንና እንሒድ” የሚል ጥያቄ በአንዳንድ የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች መቅረቡንና ዐቢይ ኮሚቴውም እንደሚያስብበት ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ “የበረከት ማሳታወሻ” በሚል ለተሠዉ ወገኖች ማዘከሪያ የተዘጋጁ የመታሰቢያ ካርዶች ሽያጭ፣ እንደ አንድ የገቢ ማስገኛ የታቀደ ሲኾን፤ ከ50 እስከ 500 ብር ዋጋ ያላቸውና ለዚሁ ዓላማ ብቻ የተቀረጸው የዐቢይ ኮሚቴው ክብ ማኅተም ያረፈባቸው 80ሺሕ ካርዶች ታትመው በሥርጭት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

JIgjiga Bereket masetawosha

በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አማካይነት የሚሠራጩት ካርዶቹ በሙሉ ለሽያጭ ሲውሉ፣ 11 ሚሊዮን ብር ያህል ገቢ ያስገኛሉ፤ ተብሏል ባለ500 ብር 10ሺሕ፣ ባለ200 ብር 10ሺሕ፣ ባለ100 ብር 20ሺሕ፣ ባለ50 ብር 40ሺሕ ካርዶች መታተማቸውንና እንዳስፈላጊነቱም ኅትመቱ ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል፡፡ በትላንቱ የገቢ ማስገኛ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ “ካርዱ በኹሉም አጥቢያዎች እንዲሠራጭ፣ ሽያጩንም እንዲያስተባብሩ የቅዱስ ፓትርያርኩም የሀገረ ስብከቱም መመሪያ ነው፤ይኼን ማድረግ አለብን፤” ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እንደ ገቢ አቅማቸው የሚያዋጡት የገንዘብ አስተዋፅኦ በቁርጥ የተደለደለ ሲኾን፣ከዚህም ከ5.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታስቧል፡፡የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እያንዳንዳቸው 4 ሚሊዮን ብር ሊሰጡ እንደወሰኑና ይህም በቅዱስ ፓትርያርኩ ቀደም ብሎ መገለጹ ታውቋል፡፡

በጊዜያዊ ርዳታ በኩል፣ ከትላንት በስቲያ በሁለት መኪና የተጫነ እህል ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተልኮ በጂግጂጋ የሚገኘው የሀገረ ስብከቱ አሰራጭ ኮሚቴ ተረክቦታል፡፡ በለበሱት ልብስ ብቻ ለሚገኙት የጅግጅጋ ወገኖች በአየጥቢያው የሚካሔደው የአልባሳት ማሰባሰብም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲኾን፣ የተሽከርካሪዎች ባለንብረቶችም፣ “ለትራንስፖርት ሲዘጋጅ ይነገረን፤ ለማጓጓዙ እንተባበራለን፤” ብለዋል፡፡

ጂግጂጋ ተጎጅዎች አካውንት

የመጠለያና የመጸዳጃ ቤቶች ሥራም መዘንጋት እንደሌለበት ያወሱት የቅሰቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ መ/ር ብርሃኑ፣ ጊዜያዊ ርዳታውም ይኹን የመልሶ ማቋቋሙ ተግባር በተቻለ መጠን በፍጥነት መከናወን እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ “በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጸመው ነገር እጅግ አሳዛኝ ቢኾንም የወንጌሉ ስጦታ ነው፡፡ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ወደፊት እናስተዋውቃለን፤ ያን መከራ ያልተቀበልነው ሌሎቻችን የተቋረጠውን አገልግሎት ማስጀመርና ምእመናኑን ማጽናናት፣ ቀጥሎ ደግሞ የተሠዉትን ካህናት ልጆች ማሳደግ፣ የምእመናኑን ቤት መገንባት፣ አብያተ ክርስቲያኑን መልሰን መሥራት አለብን፤” ያሉት የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ በታቀደና በተደራጀ መንገድ በተፈጸመው ጥፋት የክልሉ መንግሥትም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበት ሳያሰስቡ አላለፉም፡፡
አያይዘውም፣ “የክልሉ መንግሥት ድርጊቱን በበጀት ደግፎ እንዳስፈረሰ በበጀቱ ማሠራት አለበት፤ በጀቱ ለማፍረስ ሳይኾን ለመገንባትም መዋል አለበት፡፡ የፌደራል መንግሥትም ቢኾን፣ ሠርተው የሚያድሩ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ግብር መልሶ የግብር ከፋዮችን ሕይወት የቀሠፈና ሀብት ንብረታቸውን በሙሉ ያወደመውን የክልሉን መንግሥት ተጠያቂ ከማድረግ አልፎ ከክልሉ በጀት ላይ አንሥቶ በብዙ ዓመታት በከፍተኛ ትግል ያፈሩት ሀብትና ንብረት ለወደመባቸው ኢትዮጵያውያን በመክፈል ፍትሕን በገቢር እንደሚያሳየን በከፍተኛ ደረጃ እየጠበቅን ነው፤ ጉዳቱ የደረሰው የመንግሥትን ሥልጣን በያዘ አካል ነውና፤” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.