“ልዩነታችን ለማስፋት የሰራውን ያህል አንድነታችን ለማጠናከር አልሰራንም፡፡” ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/155257

“ልዩነታችን ለማስፋት የሰራውን ያህል አንድነታችን ለማጠናከር አልሰራንም፡፡” ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ
(አብመድ) የምክር ቤቶቹን የጋራ ስብሰባ ያስጀመሩት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበጀት ዓመቱን የመንግስት ዐበይት የትኩረት አቅጣጫዎች ለምክር ቤቱ አባላት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ፕሬዝዳንቷ ለምክር ቤቶቹ ባቀረቡት ንግግር 2012 ዓ.ም የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል ብለዋል፡፡ ልዩነታችንን ለማስፋት የተሰራውን ያህል አንድነታችንን ለማጠናከር አልሰራንም፤ መጪውን ሁኔታ ብሩህ ለማድረግም ውዝፍ ችግሮችን ማረም አለብን ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፡፡ “ለቀጣዩ ትውልድ ከእኛ የተሻለ ሥራ ሰርተን ማስረከብ አለብን፤ የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎቻችን ግባቸውም ሀገራዊ ክብር እና የመደመር እሳቤ መሆን ይኖረባቸዋል” ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ የ2012 ዓ.ም የመንግስት አንኳር ጉዳዮች ያሏቸውንም ሀሳቦችም አቅርበዋል፡፡
ግጭቶችን ተከትሎ የተከሰተው መፈናቀልና ችግር በታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በተሟላ መልኩ የመመለስ እና መሰል ጥፋቶች ድጋሜ እንዳይከሰቱ ለማድረግ ይሰራል፤ ግጭትን ቀድሞ የመከላከል ሥራም ይከናወናል ብለዋል፡፡
ከሰላም አኳያ ኅብረተሰቡን መሠረት ያደረጉ የሰላም ግንባታ ተግባራት እንደሚከናወኑ አቅርበዋል፡፡ የፖሊስን አቅም በሳይንሳዊ መንገድ በማሳደግ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሀገራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ በዓመቱ በትኩረት እንደሚሰራም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ለምክር ቤቶቹ አቅርበዋል፡፡
መጪውን ምርጫ በተመለከተ ባቀረቡት ሀሳብ የ2012 ምርጫ ሦስት ነገሮችን መሠረት ያደረገ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ያለፉ የምርጫ ግድፈቶችን ያረመ፣ ነጻነትና ተቀባይነት ያለው
እንዲሁም የፖለቲካ ልሂቃንን እና የሕዝብ ተሳትፎን ያረጋገጠ እንዲሆን እንደሚጠበቅ ነው ፕሬዝዳንቷ ያቀረቡት፡፡
ለዚህም የሚዲያ፣ የሲቪክ ማኅበራት እና የሌሎችም የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.