መንግስት አደጋዎችን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ “ያልተቀናጀ እና ደካማ ነው” ሲል ኢዜማ ተቸ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ መንግስት የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለመከላከል፣ ጉዳቶችን ለመቀነስ እና ተጎጂዎችን ለመቋቋም የሚወስደው እርምጃ “ያልተቀናጀ እና ደካማ ነው” ሲል ተቸ። ፓርቲው ዛሬ ረቡዕ መስከረም 6 ባወጣው መግለጫ የመንግስት ደካማ እርምጃ “የዜጎችን ስቃይ እያረዘመው ነው” ብሏል። 

የኢዜማ የዛሬው መግለጫ ያጠነጠነው የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በደረሱ ጥቃቶች እና በጎርፍ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ ነው። በሁለቱም አደጋዎች ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው እገዛ አናሳ መሆኑን በመግለጫው ያነሳው ፓርቲው መንግስት ለመልሶ ማቋቋም ስራው ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል። 

ከድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን ጥቃት እና ተጎጂዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚያጣራ ቡድን ጉዳቱ ወደተከሰተባቸው መላኩን ኢዜማ በመግለጫው ላይ አስታውሷል። አጣሪ ቡድኑ በሻሸመኔ እና አርሲ ዞን ዴራ ከተማ የደረሰውን ጉዳት ባለፈው ነሐሴው ወር አጋማሽ መመልከቱን መግለጫው አስረድቷል። ሆኖም ቡድኑ ወደ ሌሎች ቦታዎች ሊያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ በፀጥታ ስጋት ምክንያት መገደቡንም ጠቅሷል።

“የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት የነበረባቸው አካላት ሕዝቡን ከጉዳት መከላከል እየቻሉ ከለላ ባለመስጠታቸው፤ በደረሰው ጥቃት ላይ ተቋማቱ በቂ ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል ብለን አናምናለን”

– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

“ቅኝት በተደረገባቸው ቦታዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የክልሉ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሠራዊት ‘ትዕዛዝ አልደረሰንም’ በሚል ምክንያት ንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማስቆም አለመቻላቸውን ገልጸዋል” ሲል የኢዜማ መግለጫ አትቷል። “የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት የነበረባቸው አካላት ሕዝቡን ከጉዳት መከላከል እየቻሉ ከለላ ባለመስጠታቸው፤ በደረሰው ጥቃት ላይ ተቋማቱ በቂ ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል ብለን አናምናለን” ሲል ፓርቲው አቋሙን በመግለጫው ይፋ አድርጓል። 

መንግሥት በሻሸመኔ እና በአርሲ ዞን ዴራ ከተማ የሚኖሩ የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ተጠቂዎች ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማድረግ እና በቋሚነት መልሶ ማቋቋም ያደረገው ጥረት “እዚህ ግባ እንደማይባል” በቦታው ተገኝቶ የነበረው የኢዜማ አጣሪ ቡድን ማረጋገጡን ፓርቲው አስታውቋል። ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ የተመለከታቸውን ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ጠቅሶ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡን ኢዜማ ገልጿል። ሆኖም ፓርቲው እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከክልሉ መንግስት “ምላሽ አላገኘሁም” ብሏል።   

ሰው ሰራሽ ከሆነው ከዚህ አደጋ በተጨማሪ መንግስት በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እያደረገውን ያለውን ድጋፍ በተመለከተ ኢዜማ በመግለጫው ላይ አንስቷል። የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች  “የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ በከፍተኛ ቁጥር እያፈናቀለ እና ንብረት እያወደመ ይገኛል” ያለው የኢዜማ መግለጫ በአምስት ክልሎች የሚገኙ እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በማሳያነት ዘርዝሯል።   

የክረምቱ ዝናብ አሁንም ጠንክሮ መቀጠሉን የጠቆመው የኢዜማ መግለጫ፤ በጎርፍ ሳቢያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላይ መጠኑ የተለያየ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ግምቶች እንዳሉ ጠቅሷል። በዚሁ የጎርፍ አደጋ ከ400 ሺህ ሰዎች በላይ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ መተንበዩንም አንስቷል። “መንግስት የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ አደጋውን ማስቀረት አለበት” የሚል እምነቱን የገለጸው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ አካባቢዎች ከሚኖሩ ዜጎች ጋር መነጋገር እንደሚገባ አመልክቷል።

መንግሥት “በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል፣ የአደጋዎቹን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ጉዳቱ ከደረሰ በኃላ ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚወሰደው እርምጃ ያልተቀናጀ እና ደካማ ነው” ሲል የተቸው ኢዜማ፤ አደጋዎቹን ቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል። ለዚህም ጉዳዩ የሚመለከተው የፌደራል ተቋም እና በየክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፎች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልል አመራሮች አና የፌደራል መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

The post መንግስት አደጋዎችን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ “ያልተቀናጀ እና ደካማ ነው” ሲል ኢዜማ ተቸ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply