መንግስት ከፍተኛ ሹም ሽር ሊያደርግ ነው

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8A%A8%E1%8D%8D%E1%89%B0%E1%8A%9B-%E1%88%B9%E1%88%9D-%E1%88%BD%E1%88%AD-%E1%88%8A%E1%8B%AB%E1%8B%B0%E1%88%AD%E1%8C%8D-%E1%8A%90%E1%8B%8D/

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 1/2011) መንግስት በቀጣይ ሳምንት ከፍተኛ ሹም ሽር እንደሚያደርግ ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የሚወስነው ረቂቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለፓርላማ መላኩም ይፋ ሆኗል።

በሚቀጥለው ሳምንት በፓርላማ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ሕግ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ እንደሚያደርገው ተመልክቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትላንት የጸደቀውና በሚቀጥለው ሳምንት ፓርላማ ጸድቆ ስራ ላይ እንደሚውል በሚጠበቀው የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር የሚመለከተው አዋጅ ነባር መስሪያ ቤቶችን በማሸጋሸግ አዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን እንደሚጨምርም መረዳት ተችሏል።

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴሮችን ከሁለት ወደ አንድ የሚሰበስበው አዲሱ ሕግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የሚያዋህድ መሆኑም ተመልክቷል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር እንዲጣመሩ በማድረግ ሁለቱን ሚኒስትሮች ወደ አንድ የሚሰበስበው ሕግ ትምህርት ሚኒስቴርን ደግሞ በሁለት ከፍሎ አስቀምጧል።

ከትምህርት ሚኒስቴር በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስቴርን የጨመረው ሕግ አዲስ የሰላም ሚኒስቴር የሚል መስሪያ ቤትም ጨምሯል።

ይህ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ቁጥር ከ28 ወደ 20 የሰበሰበው ረቂቅ በቀጣዩ ሳምንት በፓርላማ የጸድቃል ተብሎ ተጠብቋል።

የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ አዲስ የካቢኔ ሹም ሽር እንደሚካሄድ ምንጮች ገልጸዋል።

ሹም ሽሩና ሽግሽጉ የሚካሄደው በተበወዙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን ባሉበት በሚቀጥሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ጭምር እንደሆነም ተመልክቷል።

 

 

 

 

The post መንግስት ከፍተኛ ሹም ሽር ሊያደርግ ነው appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.