መንግስት የቀሩትንም ፖለቲከኞች ሳያመነታ እንዲፈታ ተጠየቀ

Source: https://kalitipost.com/%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%80%E1%88%A9%E1%89%B5%E1%8A%95%E1%88%9D-%E1%8D%96%E1%88%88%E1%89%B2%E1%8A%A8%E1%8A%9E%E1%89%BD-%E1%88%B3%E1%8B%AB%E1%88%98%E1%8A%90/

“የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ከተፈለገ የኛ መፈታት ብቻ በቂ አይደለም”

ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና ቡራዩ “አሸዋ ሜዳ” አካባቢ በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ከእሳቸው ጋር 13 የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራሮች መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና የአካባቢው ወጣቶች ባደረጉላቸው አቀባበል በእጅጉ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ባደረጉት ንግግር፤ “ትግላችንን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንቀጥላለን፣ መንግስትም የተቀሩትን በነካ እጁ እንዲፈታ መጠየቃችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡ “አሁን ብዙ ነገር አላወራም፤ ነገ ከነገ ወዲያ ስራ ላይ እንገናኛለን” ሲሉም አክለዋል ዶ/ር መረራ፡፡
የፓርቲ ስራቸውን በሚቀጥሉበትና በፓርቲው መሰራት ስላለባቸው ጉዳዮችም በቀጣይ ቀናት ከአባላትና አመራሮች ጋር ምክክር አድርገው ውሳኔ እንደሚያሳልፉ የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ በተለይ መንግስት ባቀደው ብሄራዊ መግባባት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ከፓርቲ አባሎቻቸው ጋር እንደሚወያዩና መንግስት ለውይይት ያለው ፍላጎት እውነተኛ ከሆነ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የቡራዩና አካባቢዋ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለዶ/ር መረራ ጉዲና አቀባበል ባደረጉበት ወቅት  “መረራ ጀግናችን ነው!” በማለት ያዜሙ ሲሆን የእሳቸው ፎቶግራፍ የታተመበት ቲ-ሸርት ለብሰውና የተለያዩ ባነሮችን በመያዝ እንዲሁም የአበባ ጉንጉን አበርክተዋል፡፡
ዶ/ር መረራን መፈታት አስመለክቶ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ከሰጡ ደጋፊዎቻቸው መካከል አንዱ “መረራ ጉዲና ጀግናችን ነው፤ እሱ ሰላማዊ ታጋይ ነው፣ በመፈታቱ በጣም ደስተኞች ነን” ብሏል፡፡
ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ከተፈቱ የኦፌኮ አመራር አባላት መካከል አብደታ ነገሰ፣ ገላና ነገራ፣ ዮሱፍ አለማየሁ፣ ሂካ ተክሉ፣ ገመቹ ሻንቆ፣ መገርሳ አስፋው፣ ለሚ ኤዲቶ፣ አብዲ ታምራት እና አብዲሳ ኩምሳ ይገኙባቸዋል፡፡
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ቀሪ 8 አመራሮች የክሳቸው ጉዳይ መቀጠሉም ታውቋል፡፡
ክሳቸው ተቋርጦ ከተለቀቁ መካከል አንዱ የሆኑት የኦፌኮ የወጣቶች ሊግ ሊቀ መንበር አቶ ደስታ ዲንቃ በበኩላቸው፤ “ከእስር መፈታታችን ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር አጋዥ ይሆናል” ብለዋል፡፡ አክለውም፤ “መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ከፈለገ የኛ መፈታት ብቻ በቂ አይደለም፤ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የታሠሩ ሁሉ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል፡፡
ዶ/ር መረራን ጨምሮ በፌደራል ደረጃ ጉዳያቸው ተጣርቶ ረቡዕ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ከእስር የተለቀቁ 115 ግለሰቦች እሁድ ጥር 6 ቀን ወደ ሰንዳፋ ማዕከል ተወስደው ሠኞና ማክሰኞ እለት በህገ መንግስቱ ታሪካዊ አመጣጥና ያስገኘው ጥቅም እንዲሁም በሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ስልጠና እንደተሠጣቸው አቶ ደስታ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም እንደ ከዚህ ቀደሙ በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ የሚያደርጉትን የፖለቲካ ትግል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ደስታ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ታስረው ከነበሩ ግለሠቦች መካከል 35 ያህሉ መፈታታቸውን ጉዳዩን ከሚከታተሉ ምንጮች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል መኢአድ እና ሠማያዊ ፓርቲ በበኩላቸው፤ እስካሁን ከእስር የተለቀቀላቸው አባል እንደሌለ ለአዲስ አድማስ አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት የታሠሩ ፖለቲከኞችን መልቀቅ መጀመሩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከጠየቅናቸው የሃይማኖት አባቶች መካከል መጋቢ- ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ “መንግስት እስረኞችን መልቀቁ የሚበረታታ ነው፤ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር አጋዥ ነው” ብለዋል፡፡ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ሠብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሠንበቶ በበኩላቸው፤ “ለዚህች ሃገር ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ የሚመጣው በልዩነት ሃሣብ የቆመን ሠው በማሠርና በማንገላታት ሳይሆን በፍቅር ተቀራርቦ በመነጋገር በመሆኑ የመንግስት እርምጃ ይደገፋል ግን አሁንም ቀሪ እስረኞች አሉ፤ ያለ ማመንታት ሁሉንም ፖለቲከኞች መፍታት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
መንግስት  አሁን ከተለቀቁት 528 እስረኞች በተጨማሪ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ጉዳያቸው እየተጣራ በምህረትና በይቅርታ የሚለቀቁ እንዳሉ በመግለጫው ያመለከተ ሲሆን የእስረኞችን ሁኔታ የሚያጣራ ኮሚቴም ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡

Share this post

Post Comment