መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለው ያለው መግለጫ በተቃራኒ መንገድ እየተጓዘ እንደሆነ የሚያሳይ ዘገባ ቢቢሲ አቀረበ

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/41285

አባይ ሚዲያ ዜና

ቢቢሲ በጥር 4 ቀን 2010ዓም (Ethiopia court jails members of outlawed group Ginbot 7) በሚል ርእስ ባወጣው የዜና ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለው ያለው መግለጫ በተቃራኒ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን በዘገባው አስነብቧል።

ከአገዛዙ ጋር ይፋዊ ትግል እያካሄደ ያለውና የኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት በፈረጀው የግንቦት ሰባት ድርጅት  አባላት ናችሁ የተባሉ ኢትዮጵያውያን የእስር ፍርድ እንደተፈረደባቸው ቢቢሲ ለአለም ዘግቧል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ነጻ እንደሚለቀቁ ቢያሳውቁም ወደ 30 የሚጠጉ ግለሰቦች የግንቦት ሰባት አባል ናችሁ በሚል ክስ ቅጣት እንደተበየነባቸው ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

የግንቦት ሰባት ድርጅት መስራች ከነበሩት ውስጥ አንዱ የብሪታኒያና የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መሆናቸውን የጠቀሰው ቢቢሲ ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ግለሰቦች ከ 15 እስከ 18 አመት እስራት እንደተፈረደባቸው በዜና ዘገባው በማስፈር ይህን የፍርድ ብይን ከጠቅላይ ሚንስትሩ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለው ከሚለው መግለጫ ጋር ንጽጽራዊ ዘገባን በመስራት ለንባብ አቅርቧል።

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች የኦፌኮ አመራሮች ችሎትን ረብሻችሃል በሚል ሰበብ የስድስት ወር የእስራት ቅጣት እንደተበየነባቸውም ቢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል። አቶ በቀለ ገርባ ተቃውሞዋቸውን በዜማ ማቅረባቸው ያናደዳቸው ዳኛ ቅጣቱን መወሰናቸው ቢቢሲ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ የፖለቲካ እስረኞች እንደሌሉ ሲገልጽ መቆየቱን ያስታወሰው ቢቢሲ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስታቸው በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስር የዳረጋቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አምነው እስረኞቹም ነጻ እንደሚለቀቁ የገቡትን ቃል እስከ አሁን ድረስ እንዳልተገበሩት ገልጿል።

ከቅርብ አመታት ጀምሮ አገሪቷ ውስጥ በተቀሰቀሰ የህዝብ ቁጣ የፖለቲካ ቀውስ እየተስተዋለ መምጣቱን የዘገበው ቢቢሲ በፈረንጆቹ ዲሴምበረ  ወር በኢትዮጵያ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞችን ለማሰብ አለም አቀፍ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበረ አክሎ ዘገቧል።

Share this post

Post Comment