መከራችን የተራዘመውና የተባባሰው ጸሎተ ምሕላ ተጠናክሮ ባለመካሔዱ ነው፤ አገሪቱ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘርጋ – ቅዱስ ፓትርያርኩ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/05/22/%E1%88%98%E1%8A%A8%E1%88%AB%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%AB%E1%8B%98%E1%88%98%E1%8B%8D%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%89%A3%E1%89%A3%E1%88%B0%E1%8B%8D-%E1%8C%B8%E1%88%8E%E1%89%B0/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/05/holy-synod-ginbot2011-pat-opening.jpg

holy-synod-tik2011-opening1

 • ሊቃነ ጳጳሳት በየሀገረ ስብከታቸው ተገኝተው በራሳቸው መሪነት እንዲያካሒዱ አሳሰቡ፤
 • “ነጋ ጠባ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የቤተ ክርስቲያን ጉድለት ኾኖ መቀጠል የለበትም፤”

የ2011 ዓ.ም. ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ፣ ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ፣ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባሰሙት የጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳን ተጀምሯል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እጅግ ረቂቅ የኾነ ላዕላዊ እና መለኰታዊ ኀይለ ሥልጣን እንደተሰጠው በቃለ ምዕዳናቸው የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ችግሮች የኾኑትን፥ የምእመናን ፍልሰት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የምጣኔ ሀብት አያያዝ ጉድለት ማረም አቀበት ሊኾንበት እንደማይገባ ተናግረዋል – “ነጋ ጠባ የቤተ ክርስቲያናችን አጀንዳ ኾነው መቀጠል የለባቸውም፤” ብለዋል፡፡

ጉድለቶቹ የሚታረሙበት አሠራር እውን እንዲኾን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በጉጉት እየጠበቀ በመኾኑ፣ ምልአተ ጉባኤው ይህን ተገንዝቦ የምእመናንን ፍልሰት የሚገቱ፣ መልካም አስተዳደርን የሚያሰፍኑና ምጣኔ ሀብትን የሚያስጠብቁ ወሳኝ የለውጥ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርበት ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ህልውና የሚጨነቀውን ያህል ለአገርም ሰላምና አንድነት የመጨነቅ ድርብ ሓላፊነት እንዳለበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንጻር፣ እየተከሠተ ላለው መጠነ ሰፊ አገራዊ ችግር ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ፣ የሰላምና የአንድነት አስተምህሮ በስፋት እንዲሰጥ፣ የዕርቅና የኃዲገ በቀል ልምድ እንዲሠርጽ፣ ኹሉም የሃይማኖት አባቶች አጥብቀው እንዲሠሩ በተደጋጋሚ ቢወስንም፣ ከአኵስምና ጥቂት ገዳማትና አድባራት በቀር በኹሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ ባለመካሔዱ መከራው ሊያጥር እንዳልቻለና ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

ምንም ምን የሚሳነው የሌለ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ሰላማችንንና አንድነታችንን በአጭር ጊዜ እንዲያረጋግጥልን፥ ሕዝቡም ኹሉ፣ አገሪቱም በአጠቃላይ “እጆቿን ወደ እግዚአብሔር እንድትዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል፤ ለአፈጻጸሙም፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በየሀገረ ስብከታቸው ተገኝተው ጸሎተ ምሕላውን በራሳቸው እንዲመሩ፣ ትምህርተ ወንጌሉን እንዲሰጡ፣ ቂም በቀል እንዲከስም፣ ይቅርታ እንዲያብብ ያለማቋረጥ የሽምግልና ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የመክፈቻ ቃለ ምዕዳኑ ዐበይት ነጥቦች፡-
Holy Synod Ginbot2011 pat Opening
 • የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ የጊዜውን ፈተና አጥንቶ በኀይለ ሥልጣኑ የሚመክት ነው፤
 • ለቤተ ክርስቲያን ህልውና እና ለአገርም ሰላም የመጨነቅ ድርብ ሓላፊነት አለበት፤
 • ምሕላ እንዲደረግ፣ የሰላምና አንድነት አስተምህሮ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ወስኗል፤
 • ከአኵስምና ጥቂት ገዳማት በቀር ተጠናክሮ ባለመካሔዱ መከራው እየተባባሰ ነው
 • ሊቃነ ጳጳሳት በየሀ/ስብከታቸው ተገኝተው በራሳቸው መሪነት ማካሔድ ይገባቸዋል
 • የኃዲገ በቀል ልምድ እንዲሠርጽ ማስተማር እና ያለማቋረጥ መሸምገል አለባቸው
 • ሕዝቡ የአባቶቹን ድምፅ ተቀብሎ ይፈጽም፤ ፓርቲዎች ከልዩነት ቅስቀሳ ይቆጠቡ፤
 • ከሕፃን እስከ ሽማግሌ ሀገሪቱም በአጠቃላይ፣ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘርጋ፤

***

 • ለሓላፊ ጥቅም ሳይንበረከኩ እስከ መጥዎተ ርእስ የሚዘልቅ ራስን መካድ ያሻናል፤
 • ኀይለ ሃይማኖትን ተጠቅሞ እባቡንና ጊንጡን መርዝ አልባ እንዲኾን ማድረግ ነው፤
 • እባብና ጊንጥ-በፍቅረ ንዋይና በፍቅረ ሢመት የሚያለያዩ እኵያን መናፍስት ናቸው፤
 • ላዩ ማር ውስጡ መርዝ የኾነ፣ በጐጂነቱም የባሰ መንፈስ በግልጽ እየተስተዋለ ነው
 • በበለጠ ኀይል መመከት ያሻል፤ በጉድለት መቀጠል የሌለባቸው አጀንዳዎች አሉብን፤
 • የምእመናን ፍልሰት፣የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣የምጣኔ ሀብት አያያዝ ጉድለት…፤
 • ቅ/ሲኖዶስ እጅግ ረቂቅ ኀይለ ሥልጣን ተሰጥቶታልና ማረሙ ሊያዳግተው አይገባም
 • ምእመናን፣ የአሠራር ለውጡን በጉጉት እንደሚጠብቁ ግንዛቤ መውሰድ አለበት፡፡

***

 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቅዱስ ሲኖዶስ ለዓመታት የደከመባቸውን ኹለት ታላላቅና ኹለት መለስተኛ ሕንፃዎች ለቤተ ክርስቲያን በመመለሳቸው ከልብ እናመሰግናቸዋለን፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ምእመናን እንኳን ደስ አላችኹ!!!

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.