“መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ” አቶ ማሙሸት አማረ

Source: http://welkait.com/?p=12215
Print Friendly, PDF & Email

(ሸንቁጥ አየለ)

ልክ ከእስር ቤት እየወጣ ሳለ የመኢአድ ፕሬዝዳንትን አቶ ማሙሸት አማረን እንኳን ደስ አለህ ልለዉ ስልክ ደዉዬ ነበር:: የመለሰልኝ መልስ በጣም አስደመመኝ:: አሁንም ለትግል ያለዉ ወኔ አለመብረዱም ገረመኝ::ከአስራ ሶስት አመታት በላይ ሲታሰር ሲፈታ የኖረ ሰዉ አለወንጀሉ ታስሮ ሲፈታ ምን ሊሰማው እንደሚችል እኔ ማወቅ አልችልም:: ሆኖም እንኳን አብሮ ደስ ያለን ይለኛል ብዬ ነበር የጠበቅሁት::ሆኖም እሱ “መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ” ብሎ መለሰልኝ:: ማሙሸት አማረ አስከትሎም የሚከተለዉን ተናገረ::

አቶ ማሙሸት አማረ

“ደስተኛ ልሆን የምችለዉ ሁሉም የመኢአድ አመራሮች እና አባላት ሲለቀቁ ነዉ:: ደስተኛ የምሆነዉ ሁሉም የተቃዋሚ ሀይላት ሲለቀቁ : ሁሉም የሰበአዊ መብት ታጋይ ሲፈቱ: ሁሉም ጋዜጠኞች ሲፈቱ ብሎም በመጨረሻ ዲሞክራሲ እና ሰላም የናፈቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲን ሲጎናጸፍ ብሎም ኢትዮጵያ ወደ በለጸገ ሀገርነት ደርሳ ህዝቧ ደስተኛ ሲሆን ነዉ::መፈታቴ ደስተኛ የሚያደርገኝ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ስትፈታ ነዉ::

አሁን እኔ ተፈታሁ ብዬ ደስታ የለኝ::ምን ደስታ ይኖረኛል? መጀመሪያዉንም የታሰርሁት ያለ ወንጀሌ ነዉ::ስለ ህዝቤ ዲሞክራሲ እና መብት በመታገሌ ብቻ ነዉ የታሰርኩት::
አሁን የእኔ መፈታት ህዝቤም አብሮ ዲሞክራሲን ካላገኘ ምንም ዋጋ የለዉም::የኔ መታሰር እና መፈታት ቁምነገር አይደለም:: ስታሰር እና ስፈታ የኖርኩት ለህዝብ ዲሞክራሲ እና ሰላም ነዉ:: እናም አሁን መፈታቴ ደስተኛ ሊያደርገኝ አይችልም::ምክንያቱም ህዝባችን ዲሞክራሲ: እና እፎይታን ገና አላገኘም እና::

መኢአድን በህጋዊነት ተመርጠን እየመራን ያለን በርካታ አመራሮች አለጥፋታችን ታስረናል::ተሰደናል::መከራ ተቀብለናል::የተገደሉብንም አሉ:: ባለን ያልተጣራ መረጃ መሰረትም ከ120 በላይ የመኢአድ አመራሮች ታስረዋል::እጅግ በርካታ የመኢአድ አባላት እስር ቤት ናቸዉ:: አሁንም በርካታ አመራሮቻችን እና አባላታችን እንደታሰረ ነዉ:: እጅግ ብዙ ተቃዋሚ እና የሰበአዊ መብት ታጋይ እና ጋዜጠኞች እስር ቤት ናቸዉ:: እንደ እኔ እስር ቤቱን አይቶት የወጣ ሰዉ ይሄ ሁሉ ወገን ታስሮ ሳለ ምንም ደስተኛ ሊሆን አይችልም:: አጠቃላይ ኢትዮጵያ ከእስር መፈታት አለባት::ያኔም ህዝባችን ደስተኛ ሲሆን: ዲሞክራሲ ሲሰፍን እና ብልጽግና ያለዉ ማህበረሰብ ሲኖረን ከህዝባችን ጋር ደስተኛ እንሆናለን::”

አቶ ማሙሸት አማረ

የምታስተላልፈዉስ መልዕክት አለህ? ስል ጠየቅቅሁት::ፈጠን ብሎ ሶስት ነገሮችን እንደሚከተለዉ ተንትኖ አብራራልን::

1ኛ. ኢህአዴግ አሁን ያለዉ ብቸኛ አማራጭ አጠቃላይ እስረኞችን በመፍታት: የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ በማድረግ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲና መረጋጋት እንድትገባ ማድረግ መሆኑን መረዳት አለበት::
2ኛ. ተቃዋሚዎች እዚህ እና እዚያ ተበታትነን አሁንም በደካማ አካሄድ ህዝብ እንመራለን የምንለዉን አካሄድ ትተን: ትናንት የገባንበትን መቃቃር አስወግደን አብረን በመስራት የኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ የሚያገንበትን እና ዲሞክራሲን የሚጎናጸፍበትን ሂደት ማፋጠን አለብን::

3ኛ. አስመሳይ ተቃዋሚዎች ከአምባገነኖች ጋር በመሞዳሞድ: የአምባገነኖች ሰላይ በመሆን እና እዉነተኛዉን ትግልን ጠልፎ በመጣል የሚያደርጉትን ጸረ ህዝብ አካሄድ እንዲተዉ መገደድ አለባቸዉ:: የኢትዮጵያን ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ማዳከም እና ማጓተት በህዝብ እንደሚያስጠይቃቸዉ ማወቅ አለባቸዉ::

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.