ማንፌስቶውን ለማስፈጸም ሽፋን ሰጭ ሆነው እያገለገሉ ያሉት ተቋማት!!

Source: http://moreshinfo.com/archives/3703

መቅደላ ልዩ ዕትም

የአማራ ኽልውና የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት !!         

የወልቃይት፣ ራያና መተከል፣ እንዲሁም የሸዋ አዲስ አበባ ጉዳዮች የሀገራችንን የፖለቲካ ቁልፍ ጉዳዮች ሆነው በግልጽ እየቀረቡ ነው። ወገናችን በነዚህ የዐማራ ቁልፍ ማዕከሎች ለዓመታት ፍዳውን አይቷል። ይህ ፍዳ ግን በግልጽ በቃህ ሊባል ይገባዋል። ጉዳዩ የሀብትና የመሬት ጉዳይ ብቻ ሳሆን የኅልውና ጉዳይ ሆኖ በግልጽ ቀርቧል።  ለማንኛውም የትግል አጋርነትዎንም ለተጎዳው ወገንዎ ያሳዩ!!

 

የትግሬ ወያኔ በየካቲት 1968 ዓ.ም ባወጣው ድርጅታዊ ማንፌስቶው ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው ከሌላው የኢትዮጵያ ግዛት ተገንጥላ የምትመሰረተው “የትግራይ” የወሰን ግዛት በማንፌስቶው “መቅድም ገጽ V” ላይ እንደተቀመጠው በደቡብ ከወሎ ድፍን ራያንና በምዕራብ በኩል ከጎንደር ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ ተወስደው ወደ ትግራይ የሚጠቃለሉ መሆናቸውን
አስቀድሞ ወስኗል።

ይህን በማንፌስቶው ላይ በግልጽ የተቀመጠውን የመስፋፋት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግም ደግሞ ከድርጅቱ ምስረታው ጊዜ ጀምሮ ጭቃኔ የተሞላበት ወረራ መከናወኑ በሚገባ ይታወቃል።
በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ላይ ግልጽ የሆነ ዘር የማጥፋትና ከባድማ የማፈናቀል ጦርነትና ወረራ በ1972 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ያለ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታም በወሎ ክ/ሀገር በድፍን ራያና አካባቢው ባሉ ወገኖቻችን ላይም ጥቃቱ ዛሬም ድረስ በስፋት ተባብሶ የቀጠለ በመሆኑ የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (ዐኅኢአድ) ድርጊቱን በተደጋጋሚ ሲያወግዝ የቆየ ከመሆኑ ባሻገር የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት መውሰድ ያለባቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ጥቅምት ፲፮ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ በሚገባ አስቀምጧል።

የትግሬ ወያኔ የካቲት 1968 ዓ.ም ባወጣውና ዛሬም ድረስ ተግባራዊ እያደረገው ያለው “ድርጅታዊ ማንፌስቶው” የዐማራን ነገድ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሁሉ ለይቶ “በጨቋኝነትና በጠላትነት” ፈርጆ ያስቀመጠ በመሆኑ በዐማራ ነገድ ላይ እየተካሄደ ያለው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ሀብትና መሬት ዘረፋና ነጠቃ ከላይ በዋናነት ከተጠቀሱት አካባቢዎች አልፎና አድማሱን አስፍቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ላለፉት ፳፯ ዓመታት “ሕጋዊ ሽፋን” ተሰጥቶት ጭምር ተግብራዊ እንዲሆን ተደርጓል።

የትግሬ ወያኔ ከላይ በወረራ የያዛቸውን ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም ከወሎ ድፍን ራያና አካባቢው የትግራይ ክልል አካሎች አድርጎ ለማቅረብ እንደ “ሕጋዊ ሽፋን” የሚጠቀምባቸው መዋቅሮች በዋናነት ሁለት ናቸው።  እነሱም፦
፩ኛ/ በውሸት ትርክት ላይ በመመርኮዝ ዐማራን በጨቋኝነትና በጠላትነት በመፈረጅና ሆን ብሎ ከወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች በማግለል “የተሰኔ ሰንድ” ተብሎ የሚታወቀውን በቀጥታ “ሕገመንግስት” አድርጎ መጠቀሙ፣

 ፪ኛ/ ወታደራዊ ኃይልን መከታ በማድረግ በጎንደር የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት፣ በወሎ የራያ አዘቦ፣ ወፍላና አላማጣ በጎጃም መተከል ላይ የተደረገው ማፈናቀል፣ የሀብትና የልማት መሬቶቻችን ነጠቃና ይህን ተከትሎ የተዘረጋው የፌዴሬሽን አወቃቀር ዋናዎቹ ናቸው።
እናም የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት፣ የድፍን ራያና አካባቢው እንዲሁም በሂደት ለሙና ሰፊው የጎጃም አውራጃ የነበረው የመተከል የማንነት ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያት የተነሱና በግልጽ የሚታወቁ ቢሆንም ቅሉ እስከ አሁን ድረስ ተገቢና ሕጋዊ መፍትሄ አለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ግድያው፣ ማፈናቀሉና ሀብት ዘረፋው ይብስኑ ተባብሶ ቀጥሏል።
እንዲያውም በቅርቡ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ጉዳዪ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋራ አደረጉት በተባለው ውይይት መሰረት በነዚህ ከላይ በዝርዝር በተጠቀሱ ቦታዎች ላይ ያሉ ችግሮች ሁሉም “በሕገመንግስቱ መሰረትና ሕዝቡን ማዕከል ባድረገ መልኩ በሰላማዊ መንግድ ጥያቄው/ዎች ሊቀርብ ይገባል” ተብሏል መባሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት አለመረዳት ብቻ ሳይሆን አሁንም ከላይ በተራ ቁጥር ፩ የተጠቀሰው ዐማራውን በማግለል የተቀረጸው የተሰነው ሰነድ “ሕገመንግስት ተብዮ” እየተፈጸመ ላለው ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ሀብት ነጠቃና አጠቃላይ ሕገወጥ ድርጊቶች ሁሉ ምን ያህል “ሕጋዊ ሽፋን” ሰጭ ሆኖ እያገለገለ ያለ መሆኑ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ የሆኑትና የትግሬ ወያኔ ማዕከላዊ ኮሚቴዋ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብርሂም ኑርም “የራያ ቦታውም የትግራይ ነው፣ ሕዝቡም ትግሬ ነው” ብለው በአደባባይ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴሬሽን ምክርቤት የሚባለውም ልክ እንደ ዐማራ አግላዩ ሕገመንግስት ተብዮው ሁሉ የትግሬ ወያኔ
ጉዳይ ማስፈጸሚያና ሕጋዊ ሽፋን ሰጭ ተቋም መሆኑን አፍ አውጥቶ እየተናገረ ያለ መሆኑን ያሳያል።

ይህም ምንም እንኳ የትግሬ ወያኔ በረጅም እጆቹና በወኪሎቹ አማካኝነት የፌዴሬሽን ምክርቤት የሚባለውን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው መሆኑ ቢታወቅም ቅሉ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ ናቸው ተብለው ተሰይመው እያለ ያን ያህል ርቀው በመሄድ እየቀረበ ያለውን የማንነት ሕጋዊ ጥያቄ በማጣጣልና ትዕቢት በተሞላበት አገላለጽ ቃል
በቃል “የራያ ቦታውም የትግራይ ነው፣ ሕዝቡም ትግሬ ነው” ማለታቸው እጅግ በጣም ሕገወጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እውነተኛና ሚዛናዊ ኃላፊነት የሚሰማው ተቋም ቢኖር ኖሮ ስትዮዋ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በራሳቸው ፈቃድ ከያዙት ኃላፊነት ቦታ በአስቸኳይ ወርደው ቢፈልጉ የትግሬ ወያኔ ነፃ አውጭ ግንባር የካድሬነት ስራ የመስራት መብት እንዳላቸው ሊነገራቸው ይገባ ነበር።

ሆኖም ግን ይህ ሲሆን አልታየም። እንዲያውም የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምትና ድፍን ራያና አካባቢ ወገኖቻችን እያቀረቡ ያለውን የማንነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ በመካድና እውቅና በመንሳት “ጥያቄ አቅራቢው የዐማራ ክልል ነው፣ ሚቆረቆረው ዐማራ ክልል ነው” በሚል የትንኮሳና የጦርነት አዋጅ በሚመስል መልኩ የትግሬ ወያኔን አቋም ምንም
ሳይለውጡ እንዳወረደ አስተጋብተውታል።
ከላይ ለማመላከት እንደተሞከረው ሁሉ የፌዴሬሽ ምክርቤቱና የፌዴሬሽን ጉዳዮች ምኒስትር እንደ እነ ዶ/ር ሽፈራውና አቶ ዓባይ ፀሓዬ በመሰሉ ዐማራ ጠል ግለስቦች እጅ ለረጅም ጊዜ ተይዞ የቆየ በመሆኑ ዐማራው ከራሱ ባድማ ከመተከል በተመሳሳይ ሁኔታ ግድያ፣ መፈናቀልና ሀብት ነጠቃ እየተፈጸመበት ያለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ይባስ ብሎ ሕገመንግስታችን ነው ያሉትን የተሰነይ ሰነድ ካወጁ በኋላ አንድ ሽህ ኪሎ ሜትር የድንበር ርዝመትና ሃምሳ ሚሎሜትር ወደውስጥ በመግባት የኢትዮጵያ ለሙን የልማት መሬታችን ለሱዳን አሳልፈው የሰጡ የሀገርን ሉዐላዊነት የማይጠብቁ የትግራይ ነፃ አውጭ ወኪሎች በፈጠሩት ኢሕአዴግ ሽፋን በሀገር ላይ የፈጸሙት ክህደት በሕግ ሊያስጠይቃቸው ይገባል።
ሌላው አሳዛኝ ሁኔታ ደግሞ ጌታቸው ረዳ ጠፊ ለሆነ ገንዘብና ርካሽ ለሆነ ሹመት ሲል የራሱን ወገኖች ለትግሬ ወያኔ አሳልፎ ለመሸጥ መሞከሩ እጅግ በጣም አሳፋሪ ድርጊት ከመሆኑ ባሻገር እንደ ትልቅ መከራከሪያ ነጥብ አድርጎ ይዞት የቀረበው አስቂኝና አሳዛኝ ጉዳይ ቢኖር “ዐማራ ክልል የሚባለው የተፈጠረ በኢሕአዴግ ዘመን ሆኖ ሳለ ወልቃይትም ይሁን ራያ ከዐማራ ጋር በተያያዘ የማንነት ጥያቄ ሊያቀርቡ አይገባም” ብሎ የልጆች ጨዋታ ዓይነት ቀልድ ይዞ መቅረቡ ነው። ጌታቸው ረዳ ይህን ሲል ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በወረራ የተያዙት ወለቃይት ጠገዴ፣ ጠለምትና ድፍን ራያና አካባቢዎች እንዲሁም በሂደት ደግሞ የጎጃም ትልቁና ለሙ አውራጃ መተከል ጭራሽ በማያውቁትና ባልተሳተፉበት የተሰኔ ሕገመንግስት ሽፋን ሰጭነት ወደ ትግራይ ተካላችኋልና ትግሬ ሆናችኋል ስለተባሉ ብቻ ትግሬ ናቸው ማለቱ ምንም ያህል ዐይን ያወጣ ድንቁርና ብቻ ሳይሆን ዜጎች ስለ ራሳቸው ያላቸውን ታሪካዊ፣ ስነምግባራዊ እምነትና የማንነት መብት መጋፋትና ጫና መፍጠር መሆኑን አለመረዳቱን ያሳያል!!

የትግሬ ወያኔ የየካቲት 1968 ዓ.ም ማንፌስቶው ልክ እንደ ወልቃይትና ድፍን ራያ ሁሉ በክፉ ዓይን ውስጥ ያስገባው ሌላው የዐማራ ማዕከል ደግሞ ሸዋ ክ/ሀገርና ዋና ከተማው አዲስ አበባ ሲሆን ሸዋ ክ/ሀገር “የዐማራ ነገሥታት ማዕከል ነበር ተብሎ በትግሬ ወያኔ በጠላትነት ተፈርጆ” በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ የዜጎች ማፈናቀል፣ የሀብት፣ የመሬት ነጠቃና ዝርፊያ
እየተፈጸመበት ያለ ጭምር መሆኑ በሚገባት ስለሚታወቅ በጥቅምት ፲፰ በተደረገው የዐማራ ልጆች ሰላማዊ ሰልፍ በሸዋና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ ላለፉት ፳፯ ዓመታት እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ የመሬትና የማንነት ነጠቃ ድርጊቶችና ዐማራውን በልማት ስም ከኖረበት ባድማውና መኖሪያ ቤቱ በማፈናቀል በፕላስቲክ ቤት እንዲኖር ተፈርዶበት ወደ ዳር ተገፍቶ መጣሉና እነሱ ግን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ እየገነቡበት ያለ መሆኑን ሰልፉ አውግዞታል።

ለዚህም በሁሉ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ ግድያዎች፣ ግፎችና በደሎች በአስቸኳይ ይቆሙ ዘንድ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ሁነኛ የመፍትሄ ርምጃ እንዲወስድ በብዙ የዐማራ ከተሞች በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ግልጽ ጥያቄ ቀርቧል።  የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትም (ዐኅኢአድ) ያለውን ድርጅታዊ መዋቅር በመጠቀም በነቂስ ከወጣው ወገናችን ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፉን በማስተባበርና የራሱን ድርሻ ለመወጣት ከሕዝባችን ጋር ሆኖ ድምፁን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መልኩ ከፍ አድርጎ አሰምቷል።

በመሆኑም የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ መንግስት በጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ሕዝባችን በወልቃይት፣ ድፍን ራይና መተከል ጉዳዮች ላይ ይዞት የወጣውን የማንነት ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባ አስቸኳይና ሕጋዊ መልስ መስጠት ያስችል ዘንድ የራሳቸውን ወሳኝ እርምጃ እንዲወስዱ አሁንም በድጋሜ እንጠይቃለን።  በዚህ አጋጣሚ በትግሬ ወያኔ ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመባቸው ላሉ የአፋር ወገኖቻችንና በሐረር እየደረሰ ላለው የውኃ ጥም በዕለቱ የወጣው ሰላማዊ ሰልፈኛ የትግል አጋርነቱን ከመግልጽ ባሻገር የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ሁነኛ መፍትሔ እንዲስጣቸው ጭምር ጠይቋል!!

የዐማራ ኅልዉና መጠበቅ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነዉ!!

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.