ምርት ገበያው በነሐሴ ወር 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች አገበያየ

Source: https://fanabc.com/2019/09/%E1%88%9D%E1%88%AD%E1%89%B5-%E1%8C%88%E1%89%A0%E1%8B%AB%E1%8B%8D-%E1%89%A0%E1%8A%90%E1%88%90%E1%88%B4-%E1%8B%88%E1%88%AD-2-%E1%8A%90%E1%8C%A5%E1%89%A5-4-%E1%89%A2%E1%88%8A%E1%8B%A8%E1%8A%95-%E1%89%A5/

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 6 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በነሐሴ ወር 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በወሩ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው፥ 41 ሺህ 339 ቶን ምርቶችን ማገበያየቱን አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ ለገበያ የቀረበው ቡና በ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን፥ ካለፈው አመት አንጻርም 22 በመቶ በግብይት መጠንና 35 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ነው የተባለው።

በወሩ 5 ሺህ 115 ቶን ሰሊጥ ለገበያ ቀርቦ በ292 ነጥብ 79 ሚሊየን ብር ሲገበያይ፥ ከዚህ ውስጥ የሁመራ ሰሊጥ 70 በመቶ የግብይት መጠንና 73 በመቶ ዋጋ በማስመዝገብ ትልቁን ድርሻ ይዟል።

ግብይቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 78 በመቶ በዋጋ 115 በመቶ ሲጨምር አማካይ ዋጋውም በ19 በመቶ ከፍ ብሏል።

ለገበያ የቀረበ 1 ሺህ 386 ቶን ነጭ ቦሎቄም በ28 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን፥ ካለፈው ወር አንጻር በግብይት መጠንም ሆነ በዋጋ ቅናሽ አሳይቷል።

እንዲሁም በወሩ 7 ሺህ 498 ቶን አኩሪ አተር በ115 ነጥብ 32 ሚሊየን ብር ሲገበያይ፥ ከዚህ ውስጥ የጎጃም አኩሪ አተር 70 በመቶ የግብይት መጠንና ዋጋ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል።

በወሩ 1 ሺህ 955 ቶን አረንጓዴ ማሾ ለግብይት ቀርቦ በ58 ነጥብ 34 ሚሊየን ብር መገበያየቱንም ምርት ገበያው ገልጿል።

በወሩ በምርት ገበያው ከተገበያዩት ምርቶች ውስጥ ቡና 61 በመቶ የግብይት መጠንና 80 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል።

በተያያዘ ዜና በአማራጭነት ሲገበያዩ የቆዩት ቀይ ቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ አስገዳጅ ሆነው ግብይታቸው በምርት ገበያ በኩል ብቻ እንዲካሄድ በመወሰኑ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የምርቶቹን መምጣት እየተጠባበቀ መሆኑንም ነው የገለጸው።

ከዚህ ባለፈም ኑግ 10ኛ ምርት ሆኖ በቅርቡ ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ይቀላቀላል ብሏል ምርት ገበያው።

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.