ምክር ቤቱ የማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ

Source: https://fanabc.com/2019/05/%E1%88%9D%E1%8A%AD%E1%88%AD-%E1%89%A4%E1%89%B1-%E1%8B%A8%E1%88%9B%E1%8B%95%E1%8B%B5%E1%8A%95-%E1%8C%8D%E1%89%A5%E1%8B%AD%E1%89%B5-%E1%88%A8%E1%89%82%E1%89%85-%E1%8A%A0%E1%8B%8B%E1%8C%85%E1%8A%95/

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 39ኛ መደበኛ ስብሰባ የማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ በተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርመራ ሲደረግበት የቆየውን የማዕድን ግብይት ረቂቅ በመመልከት በአዋጅ ቁጥር 1144/2011 በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

ነባሩ የማዕድን ግብይት አዋጅ በአዲስ እንዲተካ አስፈላጊ ያደረጉ ጉዳዮችን ቋሚ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ አብራርቷል።

በዚህ መሰረትም ባለፈቃዶች አሁን ፈቃድ የሚያገኙት በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ መስተዳድሮች መሆኑን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው ፥ በፌዴራል መንግስት በውክልና ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ፈቃዶች መቅረታቸውንም አንስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው ማዕድናት ባሉበት አካባቢና በተግባር ስራውን ሊሰራ በሚችል አካል ፈቃዱ ሊሰጥ ይገባል የሚል አቋምም ወስኗል።

በተጨማሪም የከበሩ ማዕድናት የላኪነት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የወሰደ ሰው ያለገደብ የትኛውንም ዓይነት የከበሩ ማዕድናት ወደ ውጭ መላክ በመቻሉ ስራውን በውስን ሰዎች ብቻ በማሰራቱ ለሌሎች ዜጎች የስራ ዕድል ሳይከፍት መቆየቱን አስታውሷል።

አሁን የሚሰጠው ፈቃድና የብቃት የምስክር ወረቀት በማዕድን ዓይነቱ ተለይቶ እንዲሰጥ ስለሚያደርግ ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአሁኑ አዋጅ የግብይት ፈቃዱ ሁሉንም የማዕድናት ዓይነቶች ማካተቱን የተገለፀ ሲሆን፥ ህገ ወጥ የማዕድናት ዝውውር ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ላይም አስተማሪ ቅጣት እንደሚጥልም በማመልከት የተደረገው የህግ ማሻሻያ ጠንካራ ምክንያቶች እንደነበሩት መቁሟል።

የተሰጠ ፈቃድ እንዴት እንደሚሰረዝና የፈቃድ ሰጪው አካል ስልጣንና ተግባር ምን መምሰል እንዳለበት በረቂቅ አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ጉድለት እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው በምርመራው ወቅት በማግኘት የራሱን ማሻሻያዎች በማቅረብ በምክር ቤቱ እንዲፀድቅ አድርጓል።

የምክር ቤቱ አባላት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነት በአዋጁ ቦታ እንዲያገኝ አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን፥ ሪፖርቱንና የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፉ የማዕድናት ግብይት አዋጅ ዕቃ የመግዛትና የመሸጥ ዓይነት በመሆኑ የቀረቡትን አስተያየቶች እንደማያስተናግድ በመግለፅ አስተያየቶቹ በማዕድን ስራዎች አዋጅ እንደሚሸፈኑ አብራርተዋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.