ምክር ቤቱ የቀረቡለትን 10 ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ መራ

Source: https://fanabc.com/2019/10/%E1%88%9D%E1%8A%AD%E1%88%AD-%E1%89%A4%E1%89%B1-%E1%8B%A8%E1%89%80%E1%88%A8%E1%89%A1%E1%88%88%E1%89%B5%E1%8A%95-10-%E1%88%A8%E1%89%82%E1%89%85-%E1%8A%A0%E1%8B%8B%E1%8C%86%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%88%88/

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክር ቤቱ በሰው የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ደንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሌሎች 10 ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር እይታ እና ምርመራ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

በዛሬው ጉባዔው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የቀረበን የድጋፍ ሞሽን በማድመጥ አጽድቋል።

በሰው የመነገድና በህገ ወጥ መንገድ ደንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ የመከረው ምክር ቤቱ ለዝርዝር እይታ እና ምርመራ ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ለሴቶችና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በትብብር እንዲታይ ተመርቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የመድን ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም የተመለከተ ሲሆን፥ ለዝርዝር እይታ ለገቢዎችና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል፣ የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

እንዲሁም ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ጋር ለልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት እና ከአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ጋር ለዲላ-ቡሌ-ሃሮ ዋጩ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

በተጨማሪም ከነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ፈንድ ለአለም አቀፍ ልማት ጋር ለዲላ-ቡሌ-ሃሮ ዋጩ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ እና ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የመራው።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.