ሰው ተዋርዶ ሰይጣን ክብር ያገኘበት ዘመን

Source: http://www.danielkibret.com/2018/05/blog-post_26.html

የቤተ ክርስቲያናችን የገድላትና የተአምራት መጻሕፍት ሲጻፉ፣ የሰዎቹን ክብር በሚጠብቅ መንገድ ካልሆነ በቀር ችግር ደርሶባቸው ተአምር የተደረገላቸውን ሰዎች የተጸውዖ ስም አይገለጡም፣ ወይም የክርስትና ስማቸው ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሰዎቹን በስማቸው መጥራት ቢያስፈልግ እንኳን ለዝርዝር ማንነታቸው በማይመች ስም ይገለጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረግበት ዋናው ምክንያት የሰውን ልጅ ሰብአዊ ክብር(Human dignity) ለመጠበቅ ነው፡፡ እነርሱ ቢያልፉም እንኳን ልጅና ልጅ ልጅ ይኖራልና፡፡
እኅታችን ጌጤ ዋሚ ‹ሩጫን በሚከለክሉ በአጋንንት› ተያዘች ተብሎ የተለቀቀባትን ቪዲዮ ስመለከት በእምነት ስም የሚነግዱ ሰዎች የደረሱበትን ሞራላዊ ኪሣራ አየሁት፡፡ ከመጀመሪያው ሰይጣንን እየቀዱ ለገበያ ማዋል በየትኛውም የቅዱሳን ሕይወት ውስጥ የማናየው ነው፡፡ መቼም ሰይጣን እንደዚህ ዘመን በክብር መድረክ ያገኘበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህም አልፎ ልጅ፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ዓለም አቀፋዊ ተክለ ሰብእና ያላትን አትሌት በዚያ ዓይነት ክብርን በሚነካ ሁኔታ እያሰቃዩ በቪዲዮ ማሳየት ፈጽሞ የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰውነትን ማዋረድ እግዚአብሔርን ማዋረድ ነውና፡፡ አስፈላጊ ነው ካለች እርሷ ራሷ ትንገረን እንጂ ይህንን የመሰለ ቪዲዮ እንኳን ሌላው እርሷም ልታሳየን የተገባ አይደለም፡፡  

ሃይማኖት ታረደ ደሙን ውሻ ላሰው
ከንግዲህ ልብ ልብ አልተገናኘም ሰው
እንደተባለው ሆኖብን ነው እንጂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወትስ በሰውነት ክብር ላይ የሚቀልድ አልነበረም፡፡ የአንድን ሰው ‹ፈዋሽነት› ለማሳየት የሌላን ሰው ዝና፣ ክብርና ሰብአዊ መብት መከስከስ በምንም መልኩ ጸጋ እግዚአብሔርን አያመለክትም፡፡ የወንድማቸውን ክብር ለመጠበቅ ያልፈጸሙትን ፈጸምን ብለው መከራ የተቀበሉት የነ አባ መቃርስ፣ የነ እንባ መሪና፣ የነ ሙሴ ጸሊም፣ ቤተ ክርስቲያን፤ ለራሳቸው ክብር ሲሉ የወገኖቻቸውን ክብር በሚደፈጥጡ ‹አጥማቂዎች› ሲቀለድባት ማየት ያማል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የጳጳሳትን ዝውውር ከሚመለከት ይልቅ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሕግና ሥርዓት እንዲኖራቸው ቢያደርግ መልካም ነበር፡፡ ማን ያጥምቅ? የተጠማቂዎች ሰብአዊ ክብር፣ የተጠማቂዎችን መረጃ የመጠቀም መብት፣ በአደባባይ ራቁትን መቆምና ራቁትን ፎቶ የመነሣት ጉዳይ፣ የምስክርነት አሰጣጥ ሥነ ምግባር፣ የሴቶችና የሕጻናት መብቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና የአእምሮ ሕሙማን መብቶች፣ ወዘተ ሕግና ደንብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ገና ከዚህ የከፋም እናያለን፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.