ስኳር ጭኖ ወደ ኬንያ ተጉዞ በነበረው የትራንስፖርት ድርጅት ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

Source: http://www.zehabesha.com/amharic/?p=82610

(ቢቢኤን) መንግስት ለአንድ የውጭ ድርጅት የሸጠውን 44 ሺህ ኩንታል ስኳር ወደ ኬንያ ድንበር ሞያሌ ያጓጓዘው ድርጅት ክስ ሊመሰረትበት ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ለሽያጭ ውሉ መምከን መንግስት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ያደረገው የትራንስፖርት ድርጅቱን ነው፡፡ መቀመጫውን ዱባይ ያደረገ አንድ የውጭ ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት 44 ሺህ ኩንታል ስኳር በሁለት ሚሊዬን ዶላር ለመግዛት ውለታ መዋዋሉ የሚታወስ ሲሆን፣ የኬንያ መንግስት ባለው ህግ መሰረት አንድ የጭነት መኪና ከአራት መቶ ኩንታል በላይ ጭኖ ወደ ሀገሪቱ መግባት እንደማይችል በመግለጹ፣ ከኢትዮጵያ ስኳር ጭነው የመጡ መኪኖች ለሁለት ወራት ድንብር ላይ ለመቆም ተገድደው ነበር፡፡

ከሁሉት ወራት የድንበር ላይ ቆይታ በኋላ የጫኑትን ስኳር ወደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ እንዲመልሱ የተደረጉት መኪኖች ባለንብረት የሆነው ድርጅት፣ ‹‹በስኳር ኤክስፖርት የወደፊት ንግድ ላይ አሉታዊ ገጽታ ፈጥሯል፡፡ ኮርፖሬሽኑም ተዓማኒነት እንዲያጣ አድርጓል፡፡ እንዲሁም ኤክስፖርቱን አስተጓጉለዋል፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡ የስኳር ውል ስምምነቱ የተቋረጠውም በትራንስፖርተሮቹ አማካይነት ነው የሚል አቋም የያዘው መንግስት፣ ጉዳዩን ወደ ህግ ለመውሰድ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ትራንስፖርተሮቹ ስኳሩን ከገዛው ድርጅት ጋር አለመግባባት መፍተራቸው ለውሉ መቋረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡›› የሚል ሰበብ ያቀረበው መንግስት፣ ትራንስፖርተሮቹ ፈጠሩት ያለውን ችግር ግን በግልጽ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

ሀገሪቱ በከባድ የስኳር ችግር በተመታችበት ወቅት፣ መንግስት ለውጭ ምንዛሪ ሲል ብቻ 44 ሺህ ኩንታል ስኳር ለውጭ ድርጅት መሸጡ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡ በአሁን ሰዓትም በኢትዮጵያ ከባድ የስኳር ችግር መኖሩን ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ፡፡ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተከትሎ መንግስት ከታይላንድ እና አልጄሪያ 700 ሺህ ኩንታል ስኳር ለማስገባት ተገድዷል፡፡ ስኳሩ በየቀበሌው ይከፋፈላል ቢባልም እስካሁን ድረስ ግን የታየ ነገር እንደሌለ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

Share this post

Post Comment