ቅዱስ ፓትርያርኩ የበዓለ ጥምቀት ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፤ “በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት እንዲያከብሩ ኹኔታው ተመቻችቷል”

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/01/18/%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B5-%E1%8D%93%E1%89%B5%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%88%AD%E1%8A%A9-%E1%8B%A8%E1%89%A0%E1%8B%93%E1%88%88-%E1%8C%A5%E1%88%9D%E1%89%80%E1%89%B5-%E1%8C%89%E1%89%A5%E1%8A%9D%E1%89%B3/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/01/fb_img_1547727105282.jpg

fb_img_1547727105282

  • ፕሮቶኮሉ፣ ከሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጋራ የፈጠሩት አለመግባባት በምክንያት ተጠቅሷል፤
  • የመስተንግዶ ወጪ ጫና በመነሻነት ቢጠቀስም፣ ጉዞው ከጅምሩ በአግባቡ የታቀደ አልነበረም፤
  • ከጥር 5 እስከ 14 ታቅዶ የተሰናከለው ጉዞ፥ የሰላም፣ የበረከትና የገጽታ ግንባታ ይዘት ነበረው፤
  • በግለሰቦች የሚወሰኑ የፓትርያርኩን ጉዳዮች በተቋማዊነት የማሻሻል አስፈላጊነትን አሳይቷል፤
  • የቅዱስነታቸውን የፕሮቶኮል ጉዳዮች፣ በሞያተኛ ሓላፊ መምራቱም ሊታሰብበት ይገባል

***

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ፣ ራብዓይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ በዓለ ጥምቀትን በጎንደር ከተማ ለማክበር ዐቅደው ካለፈው ቅዳሜ ማለዳ አንሥቶ ማካሔድ የጀመሩት ጉብኝት ተቋርጦ ትላንት ማምሻውን በድንገት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጉ ተገለጸ፡፡
fb_img_1547708098628
ለጉብኝቱ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት፣ ቅዱስነታቸው ከ5 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በመኾን ቅዳሜ፣ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ጎንደር ደርሰው በጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ታቦር ከተሞች በካህናት፣ ሊቃውንት፣ ምእመናንና ባለሥልጣናት ደማቅ አቀባበል ቢደረግላቸውም፣ የጉብኝታቸው ዋና ዕቅድ በኾነው የጎንደር ከተማ የበዓለ ጥምቀት አከባበር ላይ ሳይገኙ ትላንት ኀሙስ፣ ጥር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
ለመርሐ ግብሩ መሰናከል ከጤንነት ኹኔታና ሎጂስቲክስ ጀምሮ የተለያዩ ጉዳዮች በአስተያየት መልክ ቢነሡም፣ በቅዱስነታቸው ፕሮቶኮል ሓላፊ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት እና በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት መካከል፣ በመስተንግዶ ወጪ ጫና ምክንያት የተፈጠረ አለመግባባት ዋናው ምክንያት እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ “የሆቴልና የመስተንግዶ ወጪውን የሚጋራን የለም፤ ያለንን ጨርሰናል፤” ብለው ሲያስታውቁ ከፕሮቶኮል ሓላፊው ጋራ አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ በትላንቱ የምሽት በረራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል – ብለዋል አንድ የልኡካኑ ባልደረባ፡፡
fb_img_1547727096315
ከጉዞው ጅማሬ በፊት፣ ሀገረ ስብከቱ የሆቴልና የመስተንግዶ ወጪ እንዲሸፍን በፕሮቶኮል ሓላፊው እንደተነገረውና ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ አቅሙ ውስን በመኾኑ እንደማይቻለው ገልጾ እገዛ ጠይቆ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ኾኖም፣ የፕሮቶኮል ሓላፊው ከሥራ ድርሻቸው ውጭ በሁሉም ነገር ላይ እየወሰኑ በሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ከተጠየቀውም በላይ ማገዝ የሚችሉ በርካታ ወገኖችን በማራቃቸውና ድጋፉ ባለመገኘቱ ለመርሐ ግብሩ መሰናከል ተጠያቂ እንደኾኑ ተገልጿል፡፡ “የፕሮቶኮል ሓላፊው ከተግባር ድርሻቸው ውጭ ራሳቸው አድራጊ ፈጣሪ ኾነው በፈጠሩት የአሠራር ችግር ፕሮግራሙ ተበላሽቷል፤” ብለዋል ሒደቱን በቅርበት የተከታተሉ ታዛቢዎች፡፡ ቀደም ሲል የጉዞውን ቅደም ተከተል በማውጣትና የሚከናወኑ ተግባራትን በመዘርዘር በቀረበው የቅዱስነታቸውን ክብርና ደረጃ የጠበቀ ዕቅድ፣ ጠቅላላ ወጪውን ለመሸፈን የሚችሉ አካላት የነበሩ ቢኾንም፣ሓላፊው በፈጠሩት የተግባቦት ክፍተት ሳቢያ ራሳቸውን እንዳገለሉ ታዛቢዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ባለሀብቶችና ታዋቂ ምእመናን በከፍተኛ በጀት ደግፈው ያቀረቡትና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረው የቀደመው የቅዱስነታቸው ጉዞ ዕቅድ፥ ከአኵስም እስከ ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ታቦር ድረስ የተዘረጋ፣ ለገዳማትና ለአብነት ት/ቤቶች የሚናኝ የቅዱስነታቸው በረከት ያለውና ከጥር 5 እስከ 14 ቀን የሚዘልቅ መንፈሳዊ ትውፊቱን የጠበቀ የዕርቀ ሰላም አባታዊ ጉብኝት እንደነበር ተገልጿል፤ በቀጣይነትም እስከ ሀገረ ኤርትራ ደብረ ቢዘን ገዳም የሚቀጥል የዕርቅና የገጽታ ግንባታ የተተለመበት እንደነበር ተመልክቷል፡፡ ኾኖም፣ የፕሮቶኮል ሓላፊው፣ የቅዱስነታቸውን ቤተሰቦች በመያዝ ከአጋዥ አካላት ጋራ ተባባሪ ባለመኾናቸው፣ ለጥያቄዎችም ወቅታዊ ምላሽ ባለመስጠትና ይብሱኑ በችኩልነትና በሐሜት የበጎ አሳቢዎችን ስም በማጥፋትና በማራቅ በፈጠሩት የተግባቦት ክፍተት ለጊዜው ሳይሳካ መቅረቱን ታዛቢዎቹ አስረድተዋል፡፡
fb_img_1547471191716
ከፕሮቶኮል ጉዳዮች ጋራ በተያያዘ፣ የቤተ ክርስቲያንንና የሕዝብን ሰላምና አንድነት ከማጠናከር አንጻር ከፍተኛ ትርጉምና ፋይዳ ያላቸው የቅዱስነታቸው እንቅስቃሴዎች ሲሰናከሉ የአሁኑ የመጀመሪያ እንዳልኾነና ቀደም ብሎም መገኘት የሚፈልጉባቸውና የሚገባቸው ዐበይት መንፈሳዊ ኹነቶች፣ በሥርዓቱ መጓደል ሳቢያ እንደታጎሉባቸውና በአግባቡ እንዳልተፈጸሙላቸው ጠቁመዋል፡፡እኒህም ችግሮች የፈጠሩት ክፍተት በድምር፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊነት ጋራ የፕሮቶኮል ሓላፊነቱንም ደርበው የያዙት አፈ መምህሩ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋራ በመኾን ብቻ የሚወስኑበትን የቅዱስ ፓትርያርኩ ጉዳዮች አሠራርን፣ በአግባቡ ገምግሞ ተቋማዊነቱን፣ ደረጃውንና ክብሩን የማስጠበቅ አስፈላጊነት እንደሚያስረግጥ አስገንዝበዋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ የሚገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 11 ታቦታት በሚወርዱበትና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የከተማው አስተዳደርና የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የውጭ እንግዶች ባሉበት በአዲስ አበባ የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት፣ ነገ ቅዳሜ ጥር 11 ቀን ተገኝተው በዓሉን የሚያከብሩበት ኹኔታ መመቻቸቱ ታውቋል፡፡

Share this post

One thought on “ቅዱስ ፓትርያርኩ የበዓለ ጥምቀት ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፤ “በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት እንዲያከብሩ ኹኔታው ተመቻችቷል”

  1. ነፃነት ዘለቀ · Edit

    በጣም አሣፋሪ ነው፡፡ ክብረ ነክም ነው፡፡ በገንዘብ ችግር የሚባለው አሳማኝ አይደለም፡፡ ቤ/ክ ሀብታም ናት፡፡ ችግሩ ሌላ መሆን አለበት፡፡

    Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.