ቋሚ ሲኖዶስ: የኮሮና ቫይረስን መስፋፋት ለመግታት፥ የትምህርት ተቋሞች ሙሉ በሙሉ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎች እና የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2020/03/25/%E1%89%8B%E1%88%9A-%E1%88%B2%E1%8A%96%E1%8B%B6%E1%88%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%AE%E1%88%AE%E1%8A%93-%E1%89%AB%E1%8B%AD%E1%88%A8%E1%88%B5%E1%8A%95-%E1%88%98%E1%88%B5%E1%8D%8B%E1%8D%8B%E1%89%B5-%E1%88%88/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2020/03/eotc-patriarchate-on-covid-19.jpg
His Grace Abune Yared General Manager of EOTC Patriarchate

ብፁዕ አቡነ ያሬድ: የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ /ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

 • ለአስቸኳይ ሥራ ከሚፈለጉት እና ጥሪ ሲደረግላቸው ከሚመጡት በቀር፥ መላው የጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ሠራተኞች፣ ሥራቸውን በየቤታቸው እያከናወኑ ይቆያሉ፤
 • የአብነት ት/ቤቶች እና ሙዓለ ሕፃናት፣ የካህናት ማሠልጠኛዎች፣ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች፥ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ያቆማሉ፤
 • ደቀ መዛሙርት እና ተማሪዎች፥ የተማሩትን በየቤታቸው እየቀጸሉ እና እያጠኑ ይሰነብታሉ፤
 • የመንበረ ፓትርያርክ ቅርሳቅርስ መምሪያ እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፥ የጉብኝት እና የንባብ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ አቁሞ ላልተወሰነ ጊዜ ይዘጋል፡፡

########

ወቅታዊውን ኮሮና ቫይረስ መስፋፋት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ /ቤት የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ጊዜ፣ በዓለም ላይ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ፣ የሰው ልጆችን ሕይወት በሞት እየቀጠፈ ያለው የኮሮና ቫይረስ ተላላፊ በሽታ፣ ለአገራችን ኢትዮጵያም ከፍተኛ ስጋት እየኾነ መምጣቱ ታምኖበት፣ ወረርሽኙን ለመቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደምንገኝ ይታወቃል፡፡

በመኾኑም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ባለባት ሕዝባዊ ሓላፊነት የተነሳ፣ ለዚኹ የመከላከል ሥራ፣ ራሱን የቻለ የተስፋ ግብረ ኃይል በማቋቋም፣ ኅብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ ለማድረግ በክፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡

በቀጣይም ከበሽታው ራስን በተገቢው መንገድ መጠበቅ እንዲቻል፣ ቋሚ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ፣ በጉዳዩ ላይ በሰፊው በመነጋገር በጊዜያዊነት መዘጋት በሚገባቸው የሥራ ክፍሎች ላይ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

 1. ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መምሪያዎች፡-

ሀ. የመንበረ ፓትርያርክ ቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ

 • ጉብኝት
 • የንባብ አገልግሎት
 1. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር ከአዲስ አበባ እስከ አህጉረ ስብከት ያሉ፡-
  ሀ. መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲዎች
  ለ. መንፈሳዊ ኮሌጆች
  ሐ. ሥልጠና ያልጀመሩ የካህናት ማስልጠኛዎች
  መ. ሙዓለ ሕፃናት
  ረ. የአብነት ትምህርት ቤቶች

ላልተወሰነ ጊዜ የመማር ማስተማሩ ሥራ አቁመው፣ ደቀ መዛሙርት እና ተማሪዎች በየቤታቸው የተማሩትን እየቀጸሉ እና እያጠኑ እንዲቆዩ፤

 1. በከፊል እንዲዘጉ የተደረጉ

ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ መላው አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች፣ ለአስቸኳይ ሥራ ከሚፈለጉ እና ተለይተው እንዲቆዩ፣ ጥሪ ሲደረግላቸውም ከሚመጡ ሠራተኞች በስተቀር፣ መላው ሠራተኞች በየቤታቸው ሥራቸውን እያከናወኑ እንዲቆዩ ወስኗል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝባችንን ከሕማም ሞትአገራችንን ከልዩ ልዩ መቅሰፍት እና ደዌ ይጠብቅልን፡፡

ብፁዕ አባ ያሬድ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ /ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና

የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም.EOTC Patriarchate on COVID 19

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.