በሀገር ሰላምና በቤተ ክርስቲያን መብቶች መጠበቅ: ቅዱስ ሲኖዶስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከክልሎች ፕሬዝዳንቶች ጋራ ይመክራል

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2018/10/30/%E1%89%A0%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%88%9D%E1%8A%93-%E1%89%A0%E1%89%A4%E1%89%B0-%E1%8A%AD%E1%88%AD%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B6%E1%89%BD/
https://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G


  • የቤተ ክርስቲያን ይዞታና መብት የአገርም እንደኾነ በማስገንዘብ እንዲከበር ያሳስባል
  • አባቶችና ሰባክያን የሚቀናጁበት፣ ዓለም አቀፍ የስብከተ ወንጌል ሥምሪት ይካሔዳል
  • ለቅዱስ ፓትርያርኩ ተጠሪ የኾነ ዐቢይ አስተባባሪ ኮሚቴ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይሠየማል፤

***

  • በሲኖዶሳዊ አንድነቱ፥የፀረ ተሐድሶ ጉባኤያት በመላ አህጉረ ስብከት እንዲቋቋሙ አሳሰበ፤
  • ለሲኖዶሳዊ እና አስተዳደራዊ አንድነት የደረሰበትን ስምምነት፣መርምሮ እንዲሰነድ አዘዘ፤
  • ከአኃት የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነቱን ለማጠንከር፣ ከመንግሥት ጋራ ይሠራል፤

***

በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እየተከሠተ በሚገኘው ግጭትና መፈናቀል በግንባር ቀደምነት እየተጠቁ ያሉትን ካህናትና ምእመናን እንዲሁም መብቶቿ እየተጣሱ እልቂትና ውድመት እየደረሰባት ያለውን ቤተ ክርስቲያን ለመታደግ ያለመ ምክክር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከክልሎች ርእሳነ ብሔራት ጋራ እንደሚካሔድ ተጠቆመ፡፡

ተጽዕኖውንና እልቂቱን ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ስሜት ቻል ብታደርገውም፣ ከቀን ቀን እየተባባሰ በመሔዱ ልትታገሠው ከማትችልበት ደረጃ መድረሱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በምልዓተ ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው ሲያመለክቱ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱም በአጀንዳው ተ.ቁ(7)፣ ሀገራዊ ሰላምና ዓለም አቀፍ የስብከተ ወንጌል ሥምሪት በሚል ርእስ ተነጋግሮበታል፡፡

ከመንግሥት የፍትሕና ጸጥታ አካላት ጋራ በቅንጅት በመሥራት ጥቃቱን አስቀድሞ ማምከንና ሥርዐተ አምልኮን ያለምንም ተጽዕኖና ስጋት ለማካሔድ የሚቻልበትን አሠራር ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲቀይስ ቅዱስነታቸው ጠይቀዋል፡፡ ከፖሊቲካ ኃይሎች ጋራ በሚኖረን ግንኙነት፣ በገለልተኛነትና በአስታራቂነት ብቻ የምንቆምበት ጊዜ እንደኾነና ሁሉንም በአባትነት መንፈስ መመልከት፣ ማስተማርና መምከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ካበረከተችው ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ አንጻር ሀብቷና ይዞታዋ የአገርም እንደኾነ የተወያየው ምልዓተ ጉባኤው፣ የመስቀል ደመራና የጥምቀት(የታቦት ማደርያ)ይዞታዎቿን በመጋፋት የሚነሣውን ውዝግብና ግጭት በምሳሌነት አንሥቷል፤ ከሚታየው የመባባስ አዝማሚያ አንጻርም፣ በአስቸኳይ የሚቆምበት ምክክር ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ማድረግ አስፈላጊ እንደኾነ ተስማምቷል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ ጥያቄው የቀረበ ሲኾን፤በሚወሰነው ጊዜ ውስጥ፣ በምልዓተ ጉባኤ ደረጃ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮች ጋራ እንዲካሔድ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል፣ የፖሊቲካ ኃይሎችን ጨምሮ ለሕዝብ ሰላምና አንድነት የሚጨነቁ ወገኖች ሁሉ፣ ለሀገር የጋራ ጉዳዮች እንዲተጉና እንዲነጋገሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን የምታስተላልፍበትና የዕቅበተ እምነት ሥራዋን የምታከናውንበት፣የስብከተ ወንጌል ሥምሪት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲካሔድ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ ታውቋል፡፡

የሚጀመርበትን ትክክለኛ ጊዜ መረጃው ባይጠቅስም፣ዝግጅቱን የሚያስተባብርና ተጠሪነቱ ለቅዱስ ፓትርያርኩ የኾነ ዐቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት የሚሠየም ሲኾን፤ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተውጣጡ ብፁዓን አባቶችን፣ ካህናትንና መምህራነ ወንጌልን በአባልነት እንደሚያቅፍ ተመልክቷል፡፡ ዐቢይ ኮሚቴው በየደረጃው የሚመለከታቸውን አካላት እያነጋገረ ተልእኮውን ያከናውናል፤ አፈጻጸሙም ለቋሚ ሲኖዶሱ በሪፖርት ቀርቦ እየተገመገመ አስፈላጊው መመሪያ በመቀበል እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

የፀረ ተሐድሶን እንቅስቃሴን በተመለከተ በተ.ቁ(14) በያዘው አጀንዳ፣ የተከናወኑ ሥራዎችን በቀረበው ሪፖርት በመገምገም፣ በሲኖዶሳዊ መዋሐድ በተረጋገጠው አስተዳደራዊ አንድነት መሠረት፣ የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ የዕቅበተ እምነት ጉባኤያት ባልተቋቋሙባቸው የሀገር ውስጥ ይኹን የውጭ አህጉረ ስብከት እንዲቋቋሙ፤ በተቋቋሙትም የማጠናከርና የክትትል ሥራ እንዲሠራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

በአጀንዳ ተ.ቁ(9)፣ ለሲኖዶሳዊ አንድነቱ መሠረት በኾነው የአባቶች ዕርቀ ሰላም ንግግር፣ባለፈው ዓመት ሐምሌ አጋማሽ በዋሽንግተን የተደረሰበትን ስምምነት ዝርዝር ይዘት 6 አባላት ባሉት የብፁዓን አባቶች ኮሚቴ ቀርቦለት በየአንቀጹ ከመረመረና በአስተማሪነቱ ሐሳብ ከተለዋወጠበት በኋላ በማጽደቅ፣ ይፋዊ የቤተ ክርስቲያን ሰነድ ኾኖ እንዲቀመጥ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ በአጀንዳ ተ.ቁ(19) ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ እና የአውሮጳ አህጉረ ስብከት የተጻፈውን ደብዳቤ ተመልክቶ፣ ለዕርቀ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር የቀረበለትን የድጋፍ ጥያቄ ለመፈጸም፣ ከመንግሥት ጋራ በቅርበት በመሥራት አስፈላጊነት ላይ ተስማምቷል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.