በህገ ወጥ መንገድ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት የሰጠው ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%88%85%E1%8C%88-%E1%8B%88%E1%8C%A5-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%8B%B5-%E1%8B%93%E1%88%88%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%89%80%E1%8D%8D-%E1%8B%A8%E1%89%B4%E1%88%8C%E1%8A%AE%E1%88%9D-%E1%8A%A0/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት የሰጠው ግለሰብ በገንዘብ እና በእስራት መቀጣቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ግለሰቡ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተሰጠ ፍቃድ ብቻ ወደ ሀገር ማስገባትና መጠቀም የሚቻለውን የቴሌኮም መሳሪያዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ሲጠቀም በመቆየቱ ነው ተብሏል።

ግለሰቡ የቴሌኮም መሳሪያውን ወደ ሀገር ለማስገባት፣ ለመጠቀም እና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው 10 የሚደርሱ ጌት ዌይ መሳሪያዎችን እንዲሁም 30 ቲፒ ሊንክ የተባሉ መሳሪያዎችን ሲጠቀም መቆየቱ ተገልጿል።

በዚህ ህገ ወጥ ተግባሩም ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም በዘረጋው መሰረተ ልማት በኩል ሳይሆን በመሳሪያዎቹ አማካኝነት በዘረጋው ኔትወርክ በኩል እንዲያልፉ አድርጓል።

በተጨማሪም ከ61 ሺህ 659 ደቂቃ በላይ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በማስተላለፍ፥ ኢትዮ ቴሌኮም ያገኝ የነበረውን ከ321 ሺህ 996 ብር በላይ እንዲያጣ በማድረጉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ግለሰቡን በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል 7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራት እና በ50 ሺህ የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.