በመተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ ከነፍሰ ገዳዮች ጥቃት ያመለጡ የአማራ ተወላጆች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበ…

በመተከል ዞን በዳንጉር ወረዳ ከነፍሰ ገዳዮች ጥቃት ያመለጡ የአማራ ተወላጆች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ጳጉሜ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽት ጀምሮ በመተከል ዞን በቡለንና ወምበራ ወረዳዎች በተለይም በኤጳር እና በመልካ ቀበሌዎች በጉምዝ ታጣቂዎችና በመንግስት ሚሊሻዎች ግብረአበርነት ያለማንም ከልካይ ከ160 በላይ በሚሆኑ አገው/አማራዎች ላይ የለየለት የጅምላ አሰቃቂ ግድያ የመፈፀሙ፣በርካቶች የመቁሰላቸው ብሎም የመፈናቀላቸው አሳዛኝ ዜና የሚታወስ ነው። 3 ሳምንታት ባልሞላ ጊዜም በተመሳሳይ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ልዩ ስሙ በንገዝ በተባለ ቀበሌ መስከረም 14 ለ15 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ የታጠቁ ነፍሰ ገዳዮችና ተባባሪዎቻቸው በአካባቢው ነዋሪ በሆኑ ንፁሀን የአማራ ተወላጆች ላይ ዘር ተኮር ግድያ መፈፀማቸው ይታወቃል። በዚህ በጥይት፣በስለትና በቀስት በተደገፈው የግፍ ግድያም 14 አማራዎች እና ንፁሀንን ከጥቃት ለመከላከል ሞክረዋል የተባሉት፣ በማንነታቸው የጉምዝ ተወላጅ የሆኑት የበንገዝ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ የአቶ ደምለውን ወንድም ጨምሮ 15 ሰዎች ተመርጠው መገደላቸውን ነዋሪዎችንና አቶ ደምለውን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል። በእለቱ ከተፈፀመው ጥቃት ያመለጡት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ወርቁ ፈንቴ የ4 ወር ህጻን ካዘሉ ባለቤታቸው ጋር ለጥቂት መትረፋቸውን አውስተዋል። አቶ ወርቁ ፈንቴ እንደሚሉት ጥቃቱ ከመድረሱ ከሳምንታት በፊት የጉምዝ ታጣቂዎችና ግብረ አበሮቻቸው፣ነዋሪዎች ያዘመሩትን ሰሊጥ መሰብሰብ እንደማይችሉና እንደሚገድሏቸው በተደጋጋሚ ማስፈራሪያ ያደርሱባቸው እንደነበር ተናግረዋል። ይህን ስጋታቸውንም ለበንገዝ ቀበሌ አስተዳዳሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ አስተዳዳሪው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የፈረሙበትን ደብዳቤ ለዳንጉር ወረዳ ማስገባታቸውን ገልፀዋል። ይሁን እንጅ ወረዳው ለ3 ቀናት ያህል ብቻ መከላከያ መላኩንና እነሱም “ነካክተው” መመለሳቸውን ያወሱት ነዋሪው በወቅቱ የቀበሌ አስተዳዳሪው ሳይቀር “በጫካ ያሉ ታጣቂዎች ከአቅሜ በላይ ናቸው፣ ለምን ጥላችሁን ትሄዳላቸው” በማለት መቃወማቸውን፣ ነገር ግን ሰሚ ማጣታቸውን ነው አቶ ወርቁ የተናገሩት። አማራው ራሱን ለመከላከል የሚያስችለው ጠንካራ በትር እንኳ እንደማይፈቀድለት የገለፁት አቶ ወርቁ አንዲት ቤተሰባቸው ተገድላ ሀዘን ላይ መሆናቸውንና ሀብት ንብረታቸው በሙሉ በዘራፊዎች ተጭኖ መወሰዱን አስታውቀዋል። የአቶ ወርቁ ፈንቴ ባለቤት ወ/ሮ የሻለም ሙላት እህታቸውን በገዳዮች የተነጠቁ ሲሆን የ4 ወር ህጻን ይዘው ማምለጣቸውንና ነገር ግን መንገድ ላይ ታጣቂዎች አግኝተዋቸው እንደነበር ገልፀው አንደኛው በጥይት ለመግደል ሲያቀባብል በጓደኛው ግልግል እንደተረፉ ተናግረዋል። ገዳዮች እህላቸውን፣የተፈጨ ድቄታቸውን፣ለንግድ ያመጡትን የተለያዩ የመጠጥ አይነቶችን በአህያ ጭነው ወደ ጫካ ሲወስዱ ማየታቸውንና ቀሪ ሀብት ንብረታቸውን በሙሉ እንዳወደሙባቸው በመግለፅ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። የ14 ዓመት ህጻንና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ልጃቸው ማስተዋል ወርቅነህ እንደተገደለችባቸው የተናገሩት ደግሞ ወ/ሮ ስንቄ መንግስቴ ይባላሉ። ወ/ሮ ስንቄ የተረፉትም ለለቅሶ ጉዳይ ወደ ማምቡክ በሄዱበት መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በስልክ ያነጋገሯት ልጃቸው የመገደላቸውን መርዶ በማግስቱ እንደተነገራቸው አውስተው አስከሬን ደርሷቸው ስርዓተ ቀብር እንደፈፀሙም አስታውቀዋል። ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች በፓዌ ወረዳ አልሙ በተባለ አካባቢ ከቤተሰብ ተጠግተው በችግር ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት በመተከል የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ እጅጉ የሁኔታውን አሳሳቢነት ህዝብ ይወቀው ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። የወረዳውና የቀበሌው የመንግስት አካላት ቀድሞውኑ መረጃ እያላቸው እና ስጋት አለብን ተብሎም እየተነገራቸው ነው ጭፍጨፋው የተፈፀመው ያሉት አቶ ደሳለኝ የፌደራል፣የአማራና የቤንሻንጉል ጉምዝን መንግስትን ህይወት ማዳን አልቻሉም ሲሉ ክፉኛ ወቅሰዋል። መንግስትም ሆነ የሚመለከተው አካል ሁሉ አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ያሳሰቡት አቶ ደሳለኝ ዘላቂ መፍትሄው ግን በጉልበትና በሴራ የተወሰደውን መተከልን ወደ ቀደመ አማራዊ እርስትነት፣ ማለትም ወደ ጎጃም መመለስና ደህንነትን ለማስከበርም ከመበታተን ይልቅ ተደራጅቶ መታገል መሆኑን አስታውቀዋል። #ከአደጋው ካመለጡ ተፈናቃይ ወገኖችና ከአቶ ደሳለኝ እጅጉ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአማራ ሚዲያ ማዕከል/AMC የዩቱብ አድራሻ የምናቀርብ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply