በመከላከያ ሰራዊትና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተቀሰቀሰ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8A%A8%E1%88%8B%E1%8A%A8%E1%8B%AB-%E1%88%B0%E1%88%AB%E1%8B%8A%E1%89%B5%E1%8A%93-%E1%89%A0%E1%8A%A6%E1%8A%90%E1%8C%8D-%E1%89%B3%E1%8C%A3%E1%89%82%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%88%98/

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 19/2011) በመከላከያ ሰራዊትና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ መቀስቀሱ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ የመንግስት ሃይል ጋር ለመዋጋት ወጣቶች ወደ ጫካ መግባታቸው ትክክለኛ ርምጃ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ፋይል

ለኢሳት በደረሰው መረጃም ከአርብ ጀምሮ በጉጂ ዞን ውጊያ ተከስቷል።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተበላሸ መምጣቱን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊቱ በኦነግ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩም ተመልክቷል።

በኦነግ ላይ የተወሰደውን ርምጃ በመቃወም በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት ሲሆን አንዳንዶቹም ወደ ጫካ መግባት መጀመራቸው ተገልጿል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ወጣቶቹ የመረጡት መንገድ እንደሚጎዳቸው በመግለጽ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ አርብ በመንግስት ሃይሎችና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ተዋጊዎች ነን ባሉት ሃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከቡሌ ሆራ ወደ ሞያሌ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱ ተመልክቷል።

የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት መንገዱን ለማስከፈት መንቀሳቀሳቸውም ተሰምቷል።

በአካባቢው ሁከትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል በተባሉት የኦነግ ታጣቂዎች ላይም በተወሰደው ርምጃ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን በመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ላይም ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

በደቡብ ኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሉፕቱ በተባለው አካባቢ የተንቀሳቀሱት የኦነግ ታጣቂዎች ባዳማጋዳ ከተባለ ስፍራ ከፍንጫዋ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውም ተመልክቷል።

ይህ ቦታ ከዞኑ ዋና ከተማ ቡሌ ሆራ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን አርብ ዕለት ውጊያው የተቀሰቀሰው ሉፕቱ በተባለ ቀበሌ እንደሆነም ከኢሳት ምንጮች መረዳት ተችሏል።

በመንግስትም ሆነ በኦነግ ሃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር በግልጽ ባይታወቅም 30 ያህል የኦነግ ታጣቂዎች ቆስለዋል።

ከመንግስት ደግሞ 7 መቁሰላቸው ተመልክቷል።

ከቆሰሉት ውስጥ ወደ ቡሌ ሆራ ሆስፒታል ከተወሰዱት 5ቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለቱ ደግሞ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል መወሰዳቸውን መረዳት ተችሏል።

በቡሌ ሆራ ማለትም በቀድሞው ሃገረ ማርያም አካባቢ ውጥረት የሰፈነ ሲሆን መንግስት አካባቢውን ለማረጋጋት በከፍተኛ ሃይል እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተመልክቷል።

 

 

 

 

The post በመከላከያ ሰራዊትና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ተቀሰቀሰ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.