በመዲናዋ በተያዘው በጀት ዓመት 16 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

Source: https://fanabc.com/2019/10/%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8B%B2%E1%8A%93%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%89%B0%E1%8B%AB%E1%8B%98%E1%8B%8D-%E1%89%A0%E1%8C%80%E1%89%B5-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B5-16-%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%88%E1%8B%B5/

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በ2012 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው16 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጸው የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከ15 እስከ 40 ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው ተደርገው ነው እየተገነቡ የሚገኙት።

ከ35 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑት የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡም በመዲናዋ ትራንስፖርት ፍሰት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በየአመቱ የመዲናዋን የትራንስፖርት ፍሰት የተሳለጠ ለማድረግ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመገንባት  ወደ ስራ የሚያስገባ መሆኑ ይታወቃል።

የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያመላክተው በ 2011 በጀት አመት 22 የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል።

ባለስልጣኑ በአሁኑ ሰዓትም በግንባታ ላይ የሚገኙ ከ 100 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እንደሚያስተዳድር ነው የባለስልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥኡማይ ወልደገብርኤል የተናገሩት።

ባለስልጣኑ ከእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥም በዚህ አመት የ16 ቱን ግንባታ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው።

መንገዶቹ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን ፥ከ 35 ኪሎ ሜትር በላይ እርዝመት የሚሸፍኑ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት ግንባታቸው ይጠናቀቃሉ ተብለው ከታሰቡት ፕሮጀክቶች ውስጥ ሀይሌ ጋርመንት፣ ቄራ ጎፋ አካባቢ፣ጀሞ 3 እንዲሁም ቃሊቲ ፣ማሰልጠኛ ፣ ቡልቡላና ቂሊንጦ አካባቢ ያሉ መንገዶች መሆናቸው ታውቋል።

የመንገድ አውታሮችን ከማስፋት በተጨማሪ የሚገነቡ መንገዶች ስፋት ትኩረት መደረጉን የገለጹት አቶ ጥኡማይ፥ይህም በመዲናዋ  የሚስተዋለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በዙፋን ካሳሁን

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.