በመዲናዋ በነገው ዕለት ሶስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራሉ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8B%B2%E1%8A%93%E1%8B%8B-%E1%89%A0%E1%8A%90%E1%8C%88%E1%8B%8D-%E1%8B%95%E1%88%88%E1%89%B5-%E1%88%B6%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%8B%B3%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8B%A8%E1%88%98/

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በነገው ዕለት ሶስት አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራሉ፡፡

አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ግንባታ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በሚገኙበት በይፋ ይጀመራሉ፡፡

በዚህም ከቦሌ ሚካኤል ቀለበት መንገድ የላይና የታች መንገድ – ቡልቡላ ካባ መግቢያ 5 ነጥብ 5 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው አንዱ ነው፡፡

ሌላኛው ከአውቶቡስ ተራ- መሳለሚያ – 18 ቁጥር ማዞሪያ አድርጎ ኮልፌ ቀለበት መንገድ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 4 ኪ.ሜ ርዝመትና 40 ሜትር የጎን ስፋት እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡

ከአውቶቢስ ተራ – 18 ቁጥር ማዞሪያ ያለው ነባር መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያለበት ነው።

በተመሳሳይ ከለገሀር በጥላሁን ገሰሰ አደባባይ እስከ ጋዜቦ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት በባለስልጣኑ የራስ ሀይል የሚገነባ ሲሆን 1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር ርዝመትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 10 ሜትር ስፋት አለው ተብሏል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከለገሀር በፍላሚንጎ ጀርባ አድርጎ ወደ ቦሌ ለመጓዝ አማራጭ መንገድ በመሆን በመስቀል አደባባይ ወደ ቦሌ ይደረግ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡

እነዚህን የመንገድ ፕሮጀክቶች በሁለት አመታት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.