በመዲናዋ የመንጃ ፍቃድ እድሳትና የቦሎ አመታዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ገለጹ

በመዲናዋ የመንጃ ፍቃድ እድሳትና የቦሎ አመታዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመንጃ ፍቃድ እድሳትና የቦሎ አመታዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ገለጹ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገባቸው የየካ እና ቂርቆስ የመንጃ ፍቃድ እድሳትና የቦሎ አመታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ወረፋና መጨናነቅ እንደበዛበት መታዘብ ችሏል።
የየካ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ቅርንጫፍ ቢሮ የቦሎ አገልግሎት በወረዳ ደረጃ በቀናት በመከፋፈል አገልግሎቱን ሲሰጥ የነበረ ሲሆን በመንጃ ፍቃድ በኩል ግን መጨናነቆች ይፈጠራሉ።
ተገልጋዮች ረዘም ላለ ሰአት ወረፋ መጠበቅና መጉላላት እንዳጋጠማቸውም ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም በመሃል አገልግሎቱን በገንዘብ እናስጨርስ የሚሉ ደላሎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የሚደርሰውን የጊዜ እንግልት ለመቅረፍም አገልግሎት አሰጣጡ ሊስተካከልና የደላሎች ጣልቃ ገብነት ሊቀረፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገባቸው ቅርንጫፎችም የማሽኖች አቅም ማነስና ቶሎ ቶሎ መቋረጥ ችግር መኖሩን ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ምክሩ፥ በመንጃ ፈቃድ እድሳት ለአንድ አመት ጊዜያዊ ወረቀት መሰጠቱን ተከትሎ ዋናውን መንጃ ፍቃድ ካርድ ለመውሰድ የሚመጡ ተገልጋዮች በፈጠሩት መጨናነቅ ችግሩ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም የአዳዲስ ማሽኖች ግዥ ለመፈጸም ጨረታ መውጣቱን አስረድተዋልል።
ቦሎ አገልግሎትን በተመለከተም እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በኮቪድ19 ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ አሁን ላይ ዳግም በመጀመሩ መጨናነቁ መፈጠሩንም ነው የተናገሩት።
የደላሎችን ህገወጥ አሰራር በተመለከተም ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ለማስቀረት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
በታሪክ አዱኛ

The post በመዲናዋ የመንጃ ፍቃድ እድሳትና የቦሎ አመታዊ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ገለጹ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply