በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የአቶ መላኩ ፋንታና ሌሎችም ባለስልጣኖች ክስ ተቋረጠ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%88%99%E1%88%B5%E1%8A%93-%E1%8B%88%E1%8A%95%E1%8C%80%E1%88%8D-%E1%89%B0%E1%8A%A8%E1%88%B0%E1%8B%8D-%E1%8B%A8%E1%8A%90%E1%89%A0%E1%88%A9%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%88%98/

በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የአቶ መላኩ ፋንታና ሌሎችም ባለስልጣኖች ክስ ተቋረጠ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ በሙስና ወንጀል ተጠርትረው በእስር ቤት የቆዩት አቶ መላኩ ፋንታ ክሳቸው እንዲቋረጥ አቃቢ ህግ ጠይቋል። አቶ መላኩ ፋንታ በሴራ ፖለቲካ እንደታሰሩ የሚያመለክቱ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቀቁ ቆይቷል። ለውጥ ፈላጊ የብአዴን የአመራር አባላትም አቶ መላኩ ከእስር እንዲፈቱ ሲወተውቱ ከርመዋል።
አቶ መላኩ በተከሰሱባቸው አብዛኛው ክሶች በፍርድ ቤት ነጻ ብሎአቸው የነበረ ቢሆንም፣ ከእስር አልተለቀቁም ነበር። ከእርሳቸው ጋር አብረው ታስረው የቆዩትና በመንግስት ቴሌቪዥን በርካታ ቦታዎችንና ካርታዎችን ይዘው መገኘታቸው ዘገባ የተሰራባቸው አቶ ገብረውሃድ ወልደ ጊዮርጊስ ክሳቸው እንደተቋረጠላቸው ታውቋል። ለረጅም አመታት የመንገዶች ባለስልጣናት ሆነው የሰሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብረኤልም ክስ ተነስቷል። ከእነዚህ ባለስልጣናት በተጨማሪ አቶ ነጋ ገብረእግዚአብሄር፣ አቶ ከተማ ከበደ፣ አቶ ጌቱ ገለቴ፣ አቶ ገብረስላሴ ገብረ፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ ኮሎኔል ሀይማኖት ተስፋዬ፣ አቶ ገምሹ በየነ፣ አቶ ፍፁም ገብረመድህን፣ ኬኬ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ጌታስ ኩባንያ፣ ኮሜት ትሬዲንግ ሀውስ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ነፃ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ክሳቸው እንዲቋረጥ አቃቢ ህግ ጥያቄ አቅርቧል።
በተጨማሪም በሙስና ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ዋስይሁን አባተ፣ አቶ አክሎክ ደምሴ፣ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል፣ አቶ ዘርፉ ተሰማ፣ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ ወይዘሮ ሰኸን ጎበና፣ አቶ ጌታቸው ነገሪ፣ አቶ ነጋ መንግስቱ፣ አቶ ሙሳ መሀመድ፣ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ፣ ኮሎኔል መላኩ ደግፌ፣ ትርሲት ከበደ፣ ገዛኸኝ ኢጀራ፣ ቤዛዓለም አክሊሉ፣ ወንድሙ መንግስቱ፣ አቶ ቢልልኝ ጣሰው እና ማህደር ገብረሃናን ክስ እንዲነሳ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መጠየቁ ታውቋል።
በሙስና ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ ከ137 በላይ ሰዎች ክሳቸው እንዲነሳ ተድርጓል።
በሌላ በኩል በሽብር ወንጀል ተከሶ በእስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ ሲፈጸምበት የቆየው የቀድሞ አንድነት ፓርቲ የሰሜን ጎንደር አመራር አንጋዉ ተገኝ ፣ የአየር ኃይል ቴክኒሻኑ አቤል ከበደ እንዲሁም ደሴ አንዳርገው ዛሬ ከእስር ተፈትተዋል።

The post በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የአቶ መላኩ ፋንታና ሌሎችም ባለስልጣኖች ክስ ተቋረጠ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.