በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ ሰው በማገት ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%88%9B%E1%8B%95%E1%8A%A8%E1%88%8B%E1%8B%8A-%E1%8C%8E%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%88%AD-%E1%8B%9E%E1%8A%95-%E1%89%B3%E1%89%BD-%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%88%9B%E1%8C%AD%E1%88%86-%E1%8B%88%E1%88%A8/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ ሰው በማገት ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በህግ እንዲቀጡ መደረጉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገስጥ አሳምናቸው በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ያለፈው ዓመት ግለሰቦች ታግተው ገንዘብ እንዲያመጡ የሚጠየቁበትና በዚህም ስጋት በርካቶች አካባቢውን ለቀው የተፈናቀሉበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ሰው በማገት ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወትና ንብረት ለአደጋ ያጋለጡ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደራጀ ዘመቻ መከናወኑንም ገልጸዋል።

በዚህም 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ በዘጠኙ ላይ ክስ ተመስርቶ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በድርጊታቸው በመጸጸት የወሰዱትን ገንዘብ መልሰው ያስረከቡ መኖራቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፥ በእርቅ ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው የተመለሱ እንዳሉም ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል በወንጀል ተጠርጥረው እጃቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ባልሆኑና በጸጥታ አካላት ላይ የተኩስ አጸፋ የወሰዱ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎቸ ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።

በቀጣይ በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ተጠርጣሪዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅትይሰራል ብለዋል።

 

በክብረወሰን ኑሩ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.