በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ ውጥረት ተከሰተ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%88%9D%E1%88%B5%E1%88%AB%E1%89%85-%E1%88%83%E1%88%A8%E1%88%AD%E1%8C%8C-%E1%8A%A0%E1%8B%88%E1%8B%B3%E1%8B%AD-%E1%8B%8D%E1%8C%A5%E1%88%A8%E1%89%B5-%E1%89%B0%E1%8A%A8%E1%88%B0%E1%89%B0/

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 15/2011)በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ ውጥረት መከሰቱ ተገለጸ።

ከሀረር ከተማ መግባትና መውጣት እንዳልተቻለም ዘግይቶ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ፋይል

በአወዳይ የተከሰተው ግጭት በአካባቢው ባሉ ስርዓት አልበኞች ከተወሰደ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ ጋር የተያያዘ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ከሃረር፣ ድሬዳዋና ወደሌሎች አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ እንዳልቻሉ መንገደኞች ለኢሳት ባደረሱት የጽሁፍ መልዕክት ላይ ገልጸዋል።

ከሃረር አወዳይ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶችን የሚያስቆሙት ስርዓት አልበኞች ተሳፋሪዎች ላይ እንግልት እየፈጸሙ መሆኑም ተመልክቷል።

ከሀረር የሚወጣ ተሽከርካሪ ባለመኖሩ ሰዉ በእግር እስከሃሮማያ ድረስ በመሄድ በመሳፈር ላይ ነው ተብሏል።

ህዝቡ መንግስት ይድረስልን የሚል ጥሪ እያቀረበ ሲሆን እስካሁን ስርዓት አልበኞቹን ለማስቆም የተወሰደ ርምጃ አለመኖሩ ተገልጿል።

ሰሞኑን በስርዓት አልበኞች ርምጃ ነዋሪው አደጋ ውስጥ በገባባት ሀረር ከተማ ውጥረቱ መቀጠሉም ታውቋል።

10 ሚሊየን ብር ካልተሰጠን ብለው የከተማዋን የውሃ መስመር የቆረጡት ስርዓት አልበኞች ነዋሪውን ለውሃ ጥም መዳረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ስርዓት አልበኞቹ የከተማዋን የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በመከልከላቸውም ሀረር ለከፍተኛ በሽታ ተጋልጣ እንደምትገኝም ተዘግቧል።

ከ30 በላይ የሀረር ከተማ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ጥቃትም ከቤታቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙና መንግስት እንዲደርስላቸው ጥሪ ማድረጋቸው ታውቋል።

The post በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይ ውጥረት ተከሰተ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.