በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የአንበጣ መንጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀበሌዎችን እንደወረረ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የምንጃር ሸንኮራ…

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የአንበጣ መንጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀበሌዎችን እንደወረረ ተገለፀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ዘገባ እንዳመለከተው የአንበጣ መንጋው የኮርማ ቀበሌ አካባቢን አስጊ በሆነ መልኩ ወሮታል። የወረዳዉ እና የከተማ አስተዳደሩ ማህበረሰብ የመከላከል ሥራም በባህላዊ ዘዴዎች እያካሄደ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የአንበጣ መንጋዉ ትናንት በግማሽ ቀን ብቻ የወረዳዉ 11 ቀበሌዎችን አዳርሶ ዉሏል ነው የተባለው። በመሆኑም መንግስትና ሁሉም የማህበረሰብ አካላት ከዚህ በላይ ከፍተኛ የመከላከል ስራ መስራት እንደሚኖርባቸው የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን አሳስቧል። በተለይም የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እና የአረርቲ ከተማ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በባህላዊ መንገድ እና በኬሚካል ርጭት የመከላከል ስራ እየተሰራ ቢሆንም ከቁጥጥር ዉጭ ወጥቶ ከዚህ በላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መንግስት በአዉሮፕላን የኬሚካል ርጭት የሚከናወንበት ሁኔታን መፍጠር አለበት ነው የተባለው። በሰሜን ሸዋ ዞን የበረሃ አንበጣ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን መንጋዉን ለመከላከል የዞኑ ግብርና መምሪያ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ የቅድመ መከላከል ስራዎችን መስራቱና ስጋት ባለባቸዉ 9 ወረዳዎች አሳሽ ባለሙያዎችን ማሰማራቱን፣64 ሺህ የተለያዩ የመርጫ መሳሪያዎች፣698 ሊትር ኬሚካል ወደ ወረዳዎች መላኩንና በተጨማሪ በቀወት ወረዳ ለአንበጣ መከላከል ስራ በሚል የአዉሮፕላን መረፊያ ቦታ ማመቻቸቱን መግለፁ ይታወሳል። በዞኑ ከመስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የአንበጣ መንጋ የተከሰተ ሲሆን ይህ መልዕክት እስከተዘጋጀበት ድረስ በ9 ወረዳዎች፣ በ24 ቀበሌዎች፣ በ47 ጎጦች ፣ በ11ሺህ ሄክታር ላይ እስከ 75 በመቶ ጉዳት አድርሷል ያለው መምሪያው የተከሰተዉን የበረሃ አንበጣ በባህላዊ እና በዘመናዊ መንገድ በመጠቀም 818 ሄክታር መሬት ላይ የመከላከል ስራ ተሰርቷል ማለቱ አይዘነጋም፡፡ የበረሃ አንበጣዉ ወደ ተለያዩ ወረዳዎችና አካባቢዎች በየጊዜዉ እየተዛመተ በመሆኑም የደረሱ ሰብሎችን በአፋጣኝ በመሰብሰብ ትብብር እንዲደረግም ጠይቋል። ለዚህም አርሶ አደሮች፣የመንግሰት ሰራተኞች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ተማሪዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲ፣ በዞኑ ዉስጥ የሚገኙ ሲቪክ ማህበራት፣በጎ አድራጊ ደርጅቶችና ማህበራትና ሌሎችም በሰብል ስብሰባዉ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply