በምእራብ ኦሮሚያ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው በመመለሳቸው 45 የመጠለያ ካምፖች ተዘጉ

Source: https://fanabc.com/2019/05/%E1%89%A0%E1%88%9D%E1%8A%A5%E1%88%AB%E1%89%A5-%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8B%AB-%E1%89%B0%E1%8D%88%E1%8A%93%E1%89%83%E1%8B%AE%E1%89%BD-%E1%8B%88%E1%8B%B0-%E1%89%84%E1%8B%AB%E1%89%B8%E1%8B%8D/

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከአዋሳኝ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተፈናሉ ዜጎች ወደ ቄያቸው በ መመለሳቸው የመጠለያ ካምፖች እየተዘጉ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፥ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የመቋቋም ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በምስራቅ እና ምእራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 82 ሺህ 823 ዜጎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ መሰራቱን ገልፀዋል።

ከእነዚህ ውስጥም አስካሁን ባለው ጊዜ 66 ሺህ 652 ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቄያቸው መመለስ መቻሉን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በፀጥታ ስጋት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ከሆኑት ምስራቅ ወለጋ፣ ምእራብ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው የነበሩ 71 ሺህ 355 ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ መሰራቱንም ገልፀዋል።

በተሰራው ስራም 63 ሺህ 15 ዜጎችን ወደ መኖሪያ ቄያቸው መመለስ መቻሉን ነው አቶ አድማሱ ያስታወቁት።

በዚህም ምክንያት ዜጎቹ በተፈናቀሉበት ጊዜ ተጠልለውበት ከነበሩት 51 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ 45 የመጠሊያ ካምፖች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም ወደ መኖሪያቸው ያልተመለሱ ተፈናቃይ ዜጎችን የመመለሱ ስራ ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚሰራ መሆኑን ነው አቶ አድማሱ ያስታወቁት።

አቶ አድማሱ አክለውም፥ የክልሉ መንግስት በህዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የኦሮሚያ ክልልን አንዲሁም የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ የሚሰራ ይሆናል ነው ያሉት።

በሙለታ መንገሻ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.