በሞያሌ በተከሰተ ችግር የሰዎች ህይወት ሲጠፋ በርካታዎች መቁሰላቸው ተነገረ

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/44137

አባይ ሚዲያ ዜና 

በሞያሌ ከተማ በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ሲገለጽ ህይወታቸው የጠፋም እንዳለ ከሚወጡ መረጃዎች መረዳት ተችሏል።

በእለተ ሰንበት በተቀሰቀሰው ግጭት መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት አገር ኬኒያም የተሰደዱ ኢትዮጵያኖች እንዳሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በከተማዋ የተፈጠረው ግጭት በገሪ ሶማሌ እና በቦረና ኦሮሞ መካከል እንደሆነ እማኞች ገልጸው ከ ቀኑ ስድስት ሰአት ገደማ የጀመረው የተኩስ ለውጥ እስከ አመሻሹ ሲሰማ እንደነበረ እማኞች በተጨማሪ ገልጸዋል።

በከተማው በነበረው ችግር በትንሹ ወደ 20 የሚደርሱ ነዋሪዎች መጎዳታቸው ሲገለጽ ሶስት ሰዎች ህይወታቸው ሊያልፍ እንደቻለ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ከወራት በፊት የመንግስት ወታደሮች በንጽኋን የሞያሌ ነዋሪዎች ላይ ቀጥታ ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው እና መገደላቸው ይታወሳል። መንግስትም ወታደሮቹ በንጽኋን ህዝብ ላይ ተኩስ የከፈቱት በስህተት እንደሆነ ጠቅሶ ድርጊቱን የፈጸሙትን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ቢገልጽም  ድርጊቱን በፈጸሙ ወታደሮችም  ሆነ የግድያውን ድርጊት እንዲፈጽሙ ትእዛዝ ባስተላለፉ የመንግስት ባለስልጣን ላይ ምንም አይነት እርምጃ እንዳልተወሰደ ይታወቃል።

 በሞያሌ በነዋሪዎች ላይ በደረሰው የአካል ጉዳት እና የህይወት መጥፋት የተሰማንን ሃዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.