በሞያሌ ግጭት ተቀሰቀሰ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%88%9E%E1%8B%AB%E1%88%8C-%E1%8C%8D%E1%8C%AD%E1%89%B5-%E1%89%B0%E1%89%80%E1%88%B0%E1%89%80%E1%88%B0/

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 29/2010) በሞያሌ ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ።

በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልና በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት የተነሳ ከሞያሌ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መሰደዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ትላንት እሁድ እንደ አዲስ ባገረሸው በዚሁ ግጭት ከሁለቱ ወገኖች የተገደሉ እንዳሉም ታውቋል።

የህወሃት አገዛዝ ግጭቱን ለማስቆም እስካሁን የወሰደው ርምጃ እንደሌለ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሞያሌ ከውጥረት መላቀቅ አልቻለችም። ግጭት የየዕለት መገለጫዋ እየሆነ ነው።

ባለፈው በህወሃት ወታደሮች 13 ሰዎች ከተገደሉበት ጊዜ አንስቶ ሞያሌ ሰላም እንደራቃት አለች።

በተለይም በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልና በኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ነዋሪውን ለሞትና ስደት እየዳረገ ሳምንታትን ዘልቋል።

በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

ጋብ እያለ የቀጠለው ግጭት ትላንት ማገርሸቱን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።

በሞያሌ ከተማ ዳርቻ ባሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደአዲስ የቀጠለው ግጭት በሶማሌ ልዩ ሃይል ታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎችም አጸፋውን በመስጠታቸው ግጭቱ መስፋፋቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ግጭት በሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል በኩል አምስት ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን ከኦሮሚያ የተገደሉ ቢኖሩም በቁጥር ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በግጭቱ ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ሸሽተው ኬኒያ መግባታቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

ሞያሌ በማያባራ ግጭት ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ርምጃ መውሰድ ያልቻለው የህወሃት አገዛዝ ትላንት እንደአዲስ ስላገረሸው ግጭት እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።

በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ በካፋ ዞን ጎጀብ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ጋዜጣው እንዳለው በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ጎጀብ አካባቢ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በተቀሰቀሰ ግጭት፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ  ንብረት ወድሟል።

የግጭቱ መነሻ የሆነው ጉዳይ በጎጀብ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች፣ የጎጀብ እርሻ ልማት ይዞታ ተከፋፍሎ ይሰጠን በማለት ለጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሳይገኝ በመቆየቱ እንደሆነ የጠቀሰው ሪፖርተር ጋዜጣ ወጣቶቹ በቁጣ በወሰዱት ርምጃ የእርሻ ልማቱን ማቃጠላቸውን ገልጿል።

ከእርሻ ልማቱ በተጨማሪ ሦስት እህል የያዙ መጋዘኖች፣ ሦስት ትራክተሮች፣ አንድ ኮምባይነር፣ ወፍጮ ቤትና የእርሻ ልማቱ ሰነዶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውም ታውቋል።

በወቅቱ ከጅማ ወደ ከፋ ዞን የሚወስደው መንገድ ለ12 ሰዓታት ያህል ተዘግቶ እንደነበርም ተገልጿል።

ይህ ሁሉ ንብረት ያወደመ ግጭት ሲፈጸም የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት የሆኑት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ምንም መረጃ የለኝም ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

The post በሞያሌ ግጭት ተቀሰቀሰ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.