በርሊን ማራቶን/ በጉጉት የሚጠበቀው የበርሊን ማራቶን ትንቅንቅ እሑድ ይደረጋል

Source: http://www.mereja.com/amharic/548010

​ በተደጋጋሚ የአለም ክብረወሰን በሚሰበርበት የበርሊን ማራቶን የፊታችን እሑድ የሚካሄድ ሲሆን ታላላቆቹ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ ፣ ኢሉድ ኪፕቾጌና ዊልሰን ኪፕሳንግ የሚያደርጉት ትንቅንቅ የአትሌቲክስ አፍቃሪውን ህዝብ ትኩረት ተቆጣጥሯል፡፡ የአለማችን ሁለተኛው ፈጣን የማራቶን ሯጭ ታላቁ አትሌት ቀነኒሳ በቀለና የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ሻምፒዮኑ ኬንያዊ ኪፕቾጌ ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ባገኙበት በዚህ ውድድር ቀነኒሳ ክብረ ወሰኑን አሻሽሎ ማሸነፍ ከቻለ በአለማችን የአትሌቲክስ ታሪክ የማራቶንን ፣ የ 5000 ሜትርንና የ 10000 ሜትር ክብረወሰንን በተመሳሳይ ወቅት መያዝ የቻለ ብቸኛው አትሌት  መሆን ይችላል፡፡ቀነኒሳ የባለፈው አመት የለንደን ማራቶንን ማሸነፍ መቻሉ ይታወሳል፡፡ ኪፕቾጌ በበኩሉ የሪዮ ኦሎምፒክን የወርቅ ሜዳልያ ከማሳካቱ በተጨማሪ የአዲዳስን “Breaking 2” የሙከራ ውድድር ይፋዊ ባልሆነ 2:00:25 ሰዓት መጨረስ የቻለ ሲሆን ከቀነኒሳ ባልተናነሰ የውድድሩን አሸናፊነት ቅድመ ግምት ማግኘት ችሏል፡፡ ሌላኛው ከፍተኛ ግምትን ያገኘው የቀድሞው የአለም ክብረ ወሰን ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ ሲሆን በ 2013 በተመሳሳይ በበርሊን ማራቶን የአለምን ክብረ ወሰን በመስበር ጭምር ያሻሻለውን ገድል የመድገም ህልምን አንግቦ ወደጀርመኗ መዲና ደርሷል፡፡ ከሶስት አመት በፊት በዚሁ ማራቶን አሸናፊ ዴኒስ ኬሜቶ የተያዘውን የ 2:02:57 የማራቶን ክብረ ወሰን ያሻሽላሉ የሚል ከፍተኛ ግምትን ያገኙት ሶስቱ ታላላቅ አትሌቶች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር የፊታችን እሑድ የታላላቅ ሚዲያዎችን ቀልብ ገዝቶ ይካሄዳል፡፡Filed under: አትሌቲክስ

Share this post

Post Comment