በርካታ እስረኞች ከእስር ተለቀቁ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%88%AD%E1%8A%AB%E1%89%B3-%E1%8A%A5%E1%88%B5%E1%88%A8%E1%8A%9E%E1%89%BD-%E1%8A%A8%E1%8A%A5%E1%88%B5%E1%88%AD-%E1%89%B0%E1%88%88%E1%89%80%E1%89%81/

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2010)

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ እንዲሁም አሕመዲን ጀበል፣አቶ ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ዛሬ ከወህኒ ተለቀቁ።

ከሳምንት በፊት እንደሚፈቱ ከተገለጸ በኋላ የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፈርሙ በመጠየቃቸውና አሻፈረኝ በማለት ንጽህናቸውን በማረጋገጣቸው የተስተጓጎለው የፍቺ ሒደት ዛሬ እውን መሆኑ ታውቋል።

እጅግ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ሕዝብ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ድረስ በመሄድ አቀባበል አድርጎላቸዋል።

በተያያዘ ዜና በትላንትናው ዕለት የተፈቱት አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ በመኖሪያቸው አዳማ ከተማ በአዳማ ስታዲየም የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ፣የዋልድባ መነኮሳት እንዲሁም እነ ንግስት ይርጋ ግን አሁንም ከእስራት እንዳልተለቀቁ ታውቋል።

ዛሬ ከቀትር በኋላ ከቃሊቲና ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የተለቀቁት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣አቶ አንዱአለም አራጌ፣አቶ ኦኬሎ አኳይ፣አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ/በቅጽል ስሙ አበበ ቀሲቶ/፣አቶ ማሙሸት አማረ፣አቶ አንዱአለም አያሌው፣ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ፣ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ጫልቱ ታከለን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ እስረኞች መሆናቸውም ታውቋል።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና ፖለቲከኛው ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔር፣ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ከሚቴ አባላት ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፣ኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋ፣ኡስታዝ መሃመድ አባተ እንዲሁም ኽሊድ ኢብራሒም በተመሳሳይ ከእስር ቤት ተለቀዋል።

ጋዜጠኞች፣ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በብዛት የተፈቱ ቢሆንም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች አሁንም በእስር ቤት ይገኛሉ።

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ፣ኮሎኔል ደምሰው አንተነህ፣ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ንግስት ይርጋ፣ዮናታን ተስፋዬን ጨምሮ አሁንም በርካታ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች እንዳልተለቀቁም ታዉቋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.