በቡርጂና በሰገን አካባቢዎች ለአንድ ወር የሚቆይ ወታደራዊ ዕዝ ተቋቋመ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%89%A1%E1%88%AD%E1%8C%82%E1%8A%93-%E1%89%A0%E1%88%B0%E1%8C%88%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%8A%AB%E1%89%A3%E1%89%A2%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%88%88%E1%8A%A0%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%8B%88%E1%88%AD/

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2011)በደቡብ ኢትዮጵያ በአማሮ ልዩ ወረዳ በቡርጂና በሰገን አካባቢዎች ለአንድ ወር የሚቆይ ወታደራዊ ዕዝ መቋቋሙ ተገለጸ።

ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር የሚዋሰኑት የደቡብ ክልል አካባቢዎች በወታደራዊ ዕዝ ኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ የተወሰነው ላለፉት ሁለት ዓመታት በህዝቡ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም መሆኑን የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።

የደቡብ ዕዝ አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ሙዜይ መኮንን ህዝብ ላይ እየተፈጸመ የመጣው ጥቃት እየተባባሰ በመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ወታደራዊ ዕዝ ተቋቁሞ ስራውን ጀምሯል ማለታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አርባምንጭ ላይ እየመከሩ ያሉት የደቡብ ክልል የጸጥታ ሃላፊዎችና የመከላከያ ሰራዊት የቀጠናው አዛዦች በሶስት አካባቢዎች እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም የሚያስችል ውሳኔ አስተላልፈዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚጎራበቱት የአማሮ ልዩ ወረዳ፣ የቡርጂና የሰገን አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ በወታደራዊ ዕዝ ኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆኑ ተወስኗል።

አማሮ ልዩ ወረዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአቅራቢያ ጉጂ ዞን እየተነሱ ጥቃት በሚፈጽሙ ሃይሎች ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች እንደተፈጸመ በሚነገረው በዚሁ ተደጋጋሚ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።

በቡርጂ ልዩ ወረዳም ከምዕራብ ጉጂ ዞን በሚነሱ ታጣቂዎች በሚፈጸም ጥቃት አካባቢው ከሰላም ጋር ተራርቆ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።

በሰገን አካባቢ ይህው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ቀጠናውን መረጋጋት አሳጥቶት መክረሙን ነው በአርባምንጩ ስብሰባ ላይ የተመለከተው።

በሶስቱም አካባቢዎች በድምሩ 300 ሰዎች ተገድለዋል። ከ40ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ የኮማንድ ፖስቱን መቋቋም በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አካባቢዎቹ በልዩ የወታደራዊ ዕዝ እንዲመሩ የተወሰነው የታጠቁ ኃይሎች በሚሰነዝሩት ጥቃት በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰዉ ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ በመምጣቱ ነው ብለዋል አቶ አንድነት።

በዚህም መሰረት ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ ወታደራዊ እዝ ተቋቁሟል ነው ያሉት ሃላፊው።

በአርባምንጩ መድረክ የተገኙት የደቡብ ዕዝ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሙዜይ መኮንን በሶስቱም አካባቢዎች ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እየተባባሰ የመጣ በመሆኑ ኮማንድ ፖስቱን ማቋቋም አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡

የሚቋቋመው ወታደራዊ ዕዝ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውርን መቆጣጠርና ማስፈታትን ጨምሮ በዜጎች ግድያና ማፈናቀል ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችንና ቡደኖችን በሕግ ጥላ ስር የማዋል ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተመልክቷል።

ወታደራዊ ዕዙ ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን በአካባቢዎቹ አስተማማኝ ሠላም እስኪረጋገጥ ድረስ የሚዘልቅ እንደሚሆንም ተገልጿል።

 

 

The post በቡርጂና በሰገን አካባቢዎች ለአንድ ወር የሚቆይ ወታደራዊ ዕዝ ተቋቋመ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.