በባሕር ዳሩ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ጉባኤ ኢትዮጵያዊነት ነግሶ ታየ ተባለ

Source: http://amharic.abbaymedia.com/archives/38245

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በባሕር ዳር በተካሄደው የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ የምክክር መድረክ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ነግሶ የዋለበት ነው ሲሉ በስፍራው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ሲሆን አጠቃላይ ሂደቱንም ታሪካዊ እና ፈር ቀዳጅ ሲሉ ገልጸውታል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ፕሬዚዳንት በሆኑት አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ ከ250በላይ የኦሮሞ  ልኡካን ቡድን ሰሞኑን ወደ ባሕር ዳር በመጓዝ ከአቻው የአማራ ክልል መስተዳድር ጋር የምክክር ጉባኤ ያካሄዱ ሲሆን በዚ ጉዳይ ላይ የተጠናቀረው ልዩ ጥንቅር እንደሚከተለው ቀርባል።

**በብሔር ተኮር ግጭት ውስጥ ብልጭ ያለ ሀገር ተኮር ብሔርተኝነት- ተስፋ

“ጠላቶቻችን ይቃጠሉ እንጂ እኛ አንድነታችን ይለመልማል እንጂ አይሻክርም” ሲሉ የኦሮሞ አባገደዎች በባህርዳር የገለጹ ሲሆን አያይዘውም “በእኛ እና በአማራ መካከል ጠላቶቻችን አማራ ትምክህተኛ ነው ኦሮሞን ደግሞ ጠባብ ነው እያሉ ለስልጣን ማራዘሚያነት ከፋፈሉን እንጂ እኛ አንድ ነን “ ሲሉ አባገዳዎቹ በስሜት ተሞልተው መናገራቸው ተገልጻል።

ይህ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ምክክር ጥልቅ ጉባኤ ከአስር በላይ የአማራ ተወላጆች በኢሉባቦር [ኢሉ-አባቦራ]ቡኖ በዴሌ በግፍ ከተገደሉ 40ቸውም ገና ሳይወጣ ፡በጥቃቱም ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በየጫካው የተበተኑትን ከ3ሺህ  በላይ የአማራ ተወላጆች ወይ ወደ ቀዪአቸው ሳይመለሱ አሊያም በቂ ማረፊያና መጠለያ እንካን ሳያገኙ የኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ የጋራ ጉባኤ እጅግ በደመቀ እና ኢትዮጵያዊነትን ማእከሉ ባደረገ ሁኔታ ያካሂዳሉ ተብሎ ባይጠበቅም የሆነው ግን በእርግጥም የማይጠበቅና ያልተገመተው ሆኖ ተገኘ።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ መሪነት ከመላው ኦሮሚያ የተውጣጡ ባለስልጣናት፣አባገዳዎች፣እውቅ አርቲስቶች፣አትሌቶች፣ባለሀባትና ወጣቶችን ያካተተው 250በላይ ልኡካን ቡድን ከአቻው የአማራ ሕዝብ ጋር የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ በየብስና በዓየር ተጉዞ ባሕር ዳር ሲገባ የሞቀና የደመቀ አቀባበል እንደተቀበለው ለማወቅ ተችላል።

ላለፉት 26ዓመታት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በተለያዩ ኦሮሚያ ክልል በተለይም በምስራቅ ኦሮሚያ፣ሀረርጌ፣አርሲ፣ባሌ፣ጅማ፣ምእራብ ኦሮሚያ በግፍ ተግደለዋል፣ተፈናቅለዋል ደብዛቸው እንዲጠፋ የተደረገ ሲሆን በተመሳሳይ ወቅትም በሁለቱ አንጋፋ ሕዝብ መካከል ህወሃት መራሹ ስርዓት የጠላትነትን ግንብ የአኖሌን ሀውልት በመገንባት፣የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት እና እርሰበርስ በማናከስ ያልሰራው ስራ፣ያልፈነቀለው ድንጋይ እንደሌለ የምንዘነጋው አይደለም።

“የኦሮሞን እና አማራን ሕዝብ አንድነትና ግንኙነት ለማሻካር፣ለማዳከምና ብሎም ለማጥፋት ለዓመታት ያህል እጅግ የተሰራበት ቢሆንም ዛሬ ግን የሁለቱ ሕዝብ ግንኙነትና አንድነት አሸናፊ ሆኖ በመውጣት እነሆ ለዛሬው መተሳሰብ ደረጃ ለመድረስ በቃ” ሲሉ የአማራው ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለእንግዶቻቸው ተናግረዋል።

“የኦሮሞና አማራ ህዝብ አንድነት በመኖር ብቻ ሳይሆን በሞትም ጭምር ነው “ያሉት ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ ሲሆኑ አክለውም”የእኛ አንድነት በመኖር ብቻ ሳይሆን በመሞትም ጭምር ነው።በአድዋ፣በሶማሌ፣በባድመ ለውድ ሀገራችን ስንል ውድ ህይወታችንን እኩል ገብረን አንድ ላይ ተቀብረናል፣ ደማችንም አንድ ላይ ለአንዲት ሀገር ፈሳል” ሲሉ የሕዝብ -ለሕዝብ ምክክር መድረክ ነፍስ ዘውረተውበታል።

በዛሬይታ ኢትዮጵያ ብሔር ተኮር ግጭትና ጦርነት የቁርስ፣ምሳ እራት ያህል ተደጋግሞ በሚታይበት ወቅት ይህን መሰል ሀገር ተኮር ብሔርተኝነት ባላንጣ በተደረገ በሁለቱ ህዝብ መካከል ሲቀጣጣል ማየት በሀገራችን እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለንን ተስፋና እምነት በእጅጉ አጠንክሮልናል ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

በባሕሩ ዳሩ ጉባኤ የኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት የመድረኩ ዋልታ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊነትን የማይላቀቁት ሱስ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ምሁራን፣የሀይማኖት መሪዎችና አባገዳዎች የአማራና ኦሮሞን ሕዝብ ታሪካዊ አንድነትና ትስስር የሚገልጽ ጥናታዊ ጽሁፍ እንደቀረበና ሰፊ ገለጻዎች እንደተደረጉ ተገልጻል።

“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ያሉት አቶ ለማ መገርሳ አያይዘውም “እኛ ኢትዮጵያዊያን ሰርገኛ ጤፍ ነን።ነጩን ጤፍ ከቀዩ ጤፍ ለመለየት የማይቻል ሰርገኛ ጤፍ ነን” በማለት የኢትዮጵያዊያኑን ታሪካዊ ትስስርና አንድነትን በአጽንኦት በገልጽ ዛሬ ዛሬ ይህ ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ ሲመጣ በዝምታ ልናየው ሳይሆን ልንከላከለው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የህወሃት መራሹ ስርዓት አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው፣ኢትዮጵያዊነት በሕዝቦች ላይ በግድ የተጫነ ማንነት ነው በሚል ያላቃረጠ ስብከትና ፕሮፖጋንዳ ምክንያት አዲሱ ትውልድ በማንነት ጥያቄና ብዣታ ውስጥ ለመዘፈቅ እንደተገደደ ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን በተለይም በሁለቱ አንጋፋ ህዝብ መካከል የተገነባው የጠላትነት ግንብ አደገኛነት ከአማራና ኦሮሞ ህልውናም አልፎ ለሀገሪታም ህልውና ከፍተኛ አደጋ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በእውቁ አርቲስት አሊ ቢራ መሪነት እነ ቀመር፣ሰማህኝ በለው፣ታደለ የመሳሰሉት ድምጻዊያን በባሕር ዳሩ የምክክር መድረክ ላይ የተገኙ ሲሆን ከወር በፊት በተመሳሳይ መልኩ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከ200 በላይ ወጣቶች/ቄሮዎች/ ጣናን ኬኛ በሚል መርህ ወደ ባህር ዳር በመጋዝ በአደጋ ላይ ያለውን የጣናን ሀይቅ በመታደግ ተግባር ላይ መሳተፋቸው የሚታወቅ ሲሆን ድርጊቱንም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የእምቦጭን አረም ለመንቀል ሳይሆን አንድነትን ለመትከል የመጡ ናቸው “ሲሉ ገልጸውታል።
በባሕሩ ዳሩ ምክክር መድረክ በህወሃት መራሹ ስርዓት አንደበት በበጎ ገጽታ እማይጠቀሰው ኢትዮጵያዊነት በኦህዴዶቹ ተስምቶ በማይታወቅ ደረጃና ሁኔታ ሲወደስና ሲዘመር ታይታል። ክስተቱንም በአድናቆት ያዩ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ሁሉ በጥርጣሬም ያዩትም ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ለማየት ቢቻልም የጉባኤው ቀጣይ እርምጃ የአማራው ክልል በተራው ወደ ኦሮሚያ ክልል በመሄድ የሚፈጸም ሁለተኛ የምክክር ጉባኤ አለ በማለት አሳውቃል።

በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦህዴድ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየወሰዳቸው ባሉት ወሳኝ እርምጃዎች ምክንያት ብዙዎች ግራ ተጋብተው ሲከራከሩ ታይተዋል። እርምጃውን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ የሚቃወሙም እንዳሉ ለማየት ተችላል። በዚህ ዙሪያ የአቶ ለማ መገርሳ አካሄድ እድምታን የሚቃኝ ዘገባ በሌላ አርእስት ስር አቅርበናል-ይከታታሉ።

Share this post

Post Comment