በብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ስርአት ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%89%A5%E1%88%84%E1%88%AB%E1%8B%8A-%E1%8B%B0%E1%88%85%E1%8A%95%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%88%B5%E1%8C%8B%E1%89%B5-%E1%88%9D%E1%88%8B%E1%88%BD-%E1%8A%A0%E1%88%B0%E1%8C%A3%E1%8C%A5-%E1%88%B5/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በተዘጋጀው የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ስርአት ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ።

ሰነዱዓለምአቀፋዊ፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች ትንተናና ስጋቶች የተዳሰሰበት ነው።

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ነቢዩ ዳኜ በውይይቱ ላይ እንዳብራሩት፥ ሀገራዊ ሰላምን ማስከበር የበርካታ ጉዳዮች ድምር ውጤት በመሆኑ በዘመናዊ አለም ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የጸጥታ ስርአት በሀገር አቀፍ ደረጃ እውን ለማድረግ ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ተነሳሽነቱን በመውሰድ ሰነዱ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።

በሰነዱ ላይ የሚደረገው ውይይት አላማም በብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችና ምላሽ አሰጣጥ ስርአት ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ በማሰብ ነው ያሉት አቶ ነቢዩ፥ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ ተሳታፊዎች የሚሰጡት ግብአትም ተካቶበት ከተሻሻለ በኋላ ለመንግስት ውሳኔ ይቀርባል ብለዋል።

እንደ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ገለጻ፥ ሰነዱ የሌሎችን አገራት ልምድ በመቀመር ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተዘጋጀ ነው።

በየተቋማቱ በተበታተነ አካሄድ ሲመራ የነበረውን የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ስርአት በተደራጀ አቅም ለመምራት ያስችላል ነው ያሉት።

መንግስት እያካሄደ በሚገኘው የጸጥታ ዘርፉ ሪፎርም በተናጥል እየተመዘገቡ ካሉት አዎንታዊ ለውጦች በሻገር የመረጃና የጸጥታ ተቋማት ተቀናጅተው በመስራት የዜጎችን ህይወት፣የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዛቸው ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።

የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ስርአት  ሰነድ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ምላሽ የሚሠጡበትን ስርአት፣ የስጋት ደረጃ አመዳደብን፣ የመረጃና የጸጥታ ተቋማት የስጋት ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትንና ሃላፊነቶችን እንዲሁም ሌሎችንም ጉዳዮች ይዳስሳል።

በሰነዱ ዙሪያ ውይይት በተካሄደበት መድረክ ባለድርሻ አካላትና ምሁራን  የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ከመድረኩ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፥ በግብአትነት የሚወሰዱ ገንቢ አስተያየቶች በሰነዱ እንደሚካተቱና ተከታታይ ውይይቶች እንደሚካሄዱም መገለፁን አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ተመልክቷል።

የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምላሽ አሰጣጥ ስርአት ከሰው ሰራሽ፣ ከሽብርና ከሌሎች ተዛማጅ የጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ ችግሮች የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ነው።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.