በታንዛንያ እስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎች ዙሪያ ምክክር ተደረገ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%89%B3%E1%8A%95%E1%8B%9B%E1%8A%95%E1%8B%AB-%E1%8A%A5%E1%88%B5%E1%88%AD-%E1%89%A4%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%88%E1%8A%99-%E1%8B%9C%E1%8C%8E%E1%89%BD-%E1%8B%99%E1%88%AA/

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በታንዛንያ የተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ።

ምክክሩ በአምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም የተመራ ሲሆን፥ የታሳሪ ቤተሰብ አባላት፣ ዘመድና ወዳጆች፣ የኤምባሲው የዳያስፖራ የስራ ክፍል አስተባባሪዎች በተገኙበት ነው የተደረገው።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ በህገ ወጥ መንገድ ለመግባት የታንዛንያን ድንበር ሲያቋርጡ በፖሊስ ተይዘው በእስር ቤቶች የሚገኙ ዜጎች ስላሉበት ሁኔታ በፕሪቶሪያ ምክክር ተደርጓል።

ከዚህ ባለፈም በታንዛንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎችን ለመደገፍና ለመመለስ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የታሳሪ ቤተሰቦች እና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ዜጎችን በሰላም ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ማበርከት ስለሚገባቸው አስተዋጽኦ መነሻ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ የተገኙ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች የሚጠየቁትን ወጪ ሸፍነው ወደ ሃገራቸው እንዲመልሱ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእያንዳንዱ እስረኛ የሚያስፈልገው ወጪ ዳሬሰላም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዝርዝር ተለይቶ እንዲቀርብና ቀጣይ ስራዎችን በዝርዝሩ መሰረት ለማከናወን ከመግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኤምባሲው በተደረሰው መግባባት መሰረት ታሳሪ ዜጎችን ለመመለስ ዳሬሰላም ከሚገኘው ኤምባሲ፣ ከተባበሩት የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማህበር እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንና መረጃዎችን በመለዋወጥ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.