በትግራይ ክልል ባለፉት 9 ወራት 38 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመን ፈቃድ ተሰጠ

Source: https://fanabc.com/2019/05/%E1%89%A0%E1%89%B5%E1%8C%8D%E1%88%AB%E1%8B%AD-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%89%A3%E1%88%88%E1%8D%89%E1%89%B5-9-%E1%8B%88%E1%88%AB%E1%89%B5-38-%E1%89%A2%E1%88%8A%E1%8B%A8%E1%8A%95-%E1%89%A5%E1%88%AD/

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ባለፉት 9 ወራት 38 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1ሺህ 258 ባለሃብቶች የኢንቨስትመን ፈቃድ ተሰጠ።

የክልሉ የከተማ ልማት፣ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን እንደገለጹት ፥በተጠቀሱት ወራቶች ለ1ሺህ 185 ፕሮጀክቶች ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ እንደነበር አንስተዋል።

ይሁንና በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ተከትሎ የስራ አፈፃፀሙ ወደ 2ሺህ 258 ማደጉን ተናግረዋል።

የተሰጡት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችም ለማኑፋክቸሪንግ 755፣ ኮንስትራክሽን 219፣ ለግብርና 218፣ ለማህበራዊ አገልግሎት 24፣ ለሆቴልና ቱሪዝም 22 እንዲሁም ለማዕድን 20 መሆናቸውን አብራርተዋል።

በካፒታል ደረጃ ሲታይም በማኑፋክቸሪንግ 32 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፣ በግብርና 1 ነጥብ 76 ቢሊየን ብር፣ በሆቴልና ቱሪዝም 1 ነጥብ 17 ቢሊየን፣ በኮንስትራክሽን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር፣ በማህበራዊ አገልግሎት 209 ነጥብ 6 ሚሊየን እንዲሁም በማዕድን 240 ሚሊየን ብር መሆኑ ነው የተገለፀው።

ፕሮጀክቶቹ በቋሚነት ለ143 ሺህ 530 ዜጎች እንዲሁም 47 ሺህ 561 ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የስራ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም በእጥፍ መጨመሩን አቶ ሃፍቶም ገልፀዋል።

በደስታ ተካ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.