በአብየ ግዛት የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል የቆይታ ጊዜ ተራዘመ

Source: https://fanabc.com/2018/11/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%8B%AC-%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%88%9D-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%8A%A8%E1%89%A3%E1%88%AA-%E1%8A%83%E1%8B%AD%E1%88%8D-%E1%8B%A8%E1%89%86%E1%8B%AD%E1%89%B3-%E1%8C%8A/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2011(ኤፍቢሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአብየ ግዛት የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን አስታወቀ፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔውን ያሳለፈው ትናንት ባደረገው ስብስባ ነው ተብሏል፡፡

በተመድ የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ቋሚ መልዕክተኞች በጉዳዩ ዙሪያ ንግግር አድርገዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በአብየ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር እያበረከተችው ላለው ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በአብየ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል የአካባቢው ማህበረሰብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ በማድረግ በኩል የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አብየ ግዛት ደቡብ ሱዳንና ሰሜን ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱበት ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተልዕኮ ላይ 50 የፖሊስ አባላትን ጨምሮ 5 ሺህ 326 ወታደሮች በስፍራው ይገኛሉ።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.