በአትሌቶች ማናጀሩ ሁሴን ማኪ ላይ የተላለፈው ቅጣት ወደ ገንዘብ ተቀየረ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%88%8C%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%88%9B%E1%8A%93%E1%8C%80%E1%88%A9-%E1%88%81%E1%88%B4%E1%8A%95-%E1%88%9B%E1%8A%AA-%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%8B%E1%88%88/

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቶች ማናጀሩ ሁሴን ማኪ ላይ የተላለፈው ቅጣት ወደ ገንዘብ መቀየሩን አስታወቀ።

ፌዴሬሽኑ በዶሀው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ውድድር የተሳተፉ አትሌቶች ከማገገሚያው ሶስት ወራት በፊት ውድድር እንዳያደርጉ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወቃል።

ይሁንና የኢላይት ስፖርት ማኔጅመንት የተወሰኑ አትሌቶችን በኒውዮርክ ማራቶን ውድድር ላይ ማሳተፉን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ከማናጀሩ ሁሴን ማኪ ጋር የነበረውን ውል ማቋረጡን አስታውቆ ነበር።

ማናጀሩም የይቅርታ ደብዳቤያቸውን ለፌዴሬሽኑ በማስገባት ከሚኖሩበት አሜሪካ በመምጣት ፌዴሬሽኑን በአካል ይቅርታ ጠይቀዋል።

ፌዴሬሽኑም ጥያቄያቸውን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በኩል ከመረመረ በኋላ ይቅርታቸውን ተቀብሎ እርምጃው ለሌሎች አስተማሪ ይሆን ዘንድ ወደ ገንዘብ ቀይሮላቸዋል።

በዚህም ማናጀሩ 25 ሺህ ዶላር ቅጣት እንዲከፍሉ ውሳኔ ማሳለፉን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.