በአዲስ አበባ ከተማ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን መደገፍ የሚያስችል ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ተቋቋመ

Source: https://fanabc.com/2019/01/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9B-%E1%8A%91%E1%88%AF%E1%89%B8%E1%8B%8D%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%8C%8E%E1%8B%B3%E1%8A%93-%E1%88%8B%E1%8B%AD/

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችንና ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡትን መደገፍ የሚያስችል ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ተቋቋመ።

ፈንዱ በዛሬው እለት ይፋ የተደረገ ሲሆን፥ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂ መሆናቸው ተገልጿል።

ፈንዱ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን፣ ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የአዕምሮ ህሙማንን እና ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በከፈተው ልዩ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ተቀማጭ የሚሆን ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ነው።

የፈንዱ ምንጭም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውስጥ ገንዘብ ድጋፍ፣ ከህብረተሰቡ የሚሰጥ ድጋፍ፣ ከንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጥ ድጋፍ እና ከተለያዩ ዜጎች የሚሰጥ ልዩ ልዩ ድጋፍ ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም ከሃገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ለጋሾች የሚሰበሰብና ከተለያዩ የፋይናንስ ምንጮች የሚገኝ ነው።

ለፈንዱ ማስጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 60 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

በፈንዱ ላይ ሁሉም ዜጎች እንዲሳተፉበትም 6400 የአጭር የፅሁፍ መልዕክት መላኪያ ቁጥር ይፋ ሆኗል።

በፈንዱ አማካኝነት በአጭር ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 50 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማንሳት ይጀመራል ተብሏል።

 

 

በአላዛር ታደለ

 

Share this post

One thought on “በአዲስ አበባ ከተማ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን መደገፍ የሚያስችል ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ተቋቋመ

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.