በአዲስ አበባ የወተት እጥረት አሳሳቢ ሆነ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%8B%A8%E1%8B%88%E1%89%B0%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8C%A5%E1%88%A8%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%88%B3%E1%88%B3%E1%89%A2-%E1%88%86%E1%8A%90/

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2010) በአዲስ አበባ የወተት እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ።

ፋይል

መስተዳድሩ እጦቱ የተከሰተው የከብቶች መኖ አቅርቦት ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ መሆኑን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የወተት አቅርቦት እጥረት መከሰቱን ነው የመዲናይቱ አዲስ አበባ ነዋሪዎች የተናገሩት።

እጥረቱን ተከትሎም በወተት ዋጋ ላይ እስከ ሃምሳ በመቶ ጭማሪ መከሰቱን ነው የኢሳት ወኪሎች ያነጋገሯቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የገለጹት።

የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ የወተት እጥረት መከሰቱን የመንግስት ልሳን ለሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አረጋግጠዋል።

እጥረቱ የተከሰተው በመዲናዋ የከብቶች መኖ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ምክንያት የወተት ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት።

አቶ መስፍን እንደሚሉት የወተት አቅርቦት እጥረትን ለመቀነስ የከተማ ግብርናን የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።

የቢሮ ሃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ ኢሳት ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አስተዳደሩ ባለፉት 27 አመታት በመቶሺዎች የሚጠጉ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ገበሬዎችን መሬት በመንጠቅ የፈጸመውን ወንጀል ለአብነት በማንሳት የሃላፊውን ሃሳብ አጣጥለውታል።

የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ሃላፊው መናገራቸውም ቢሆን መፍትሄ የሚያመጣ ነገር አይደለም ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በአዲስ አበባ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት እየተለመደ በመምጣቱ ስኳር፣ዘይት፣ዳቦ፣እንቁላል፣ወተት፣ዱቄት፣እንጀራና የመሳሰሉ ሸቀጦች አቅርቦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ ርሃብ ምክንያት ከውጭ ተገዝቶ ይገባል የተባለው 400ሺ ኩንታል ስንዴ ባለመገዛቱ ምክንያትና ተያያዥ ጉዳዮች የኑሮ ውድነቱ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትልበት ደረጃ እየደረሰ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

The post በአዲስ አበባ የወተት እጥረት አሳሳቢ ሆነ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.