በአገዛዙ የፖሊስና የሚሊሺያ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8C%88%E1%8B%9B%E1%8B%99-%E1%8B%A8%E1%8D%96%E1%88%8A%E1%88%B5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%88%8A%E1%88%BA%E1%8B%AB-%E1%89%B3%E1%8C%A3%E1%89%82%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%88%8B/

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 5/2010)

በጎንደር ጯሂት በአገዛዙ የፖሊስና የሚሊሺያ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።
10 የአገዛዙ ሃይሎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ካለው የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

ከባህርዳር ወደ ኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚጓዙ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶቡሶች ስራ አቁመው መዋላቸው ታውቋል።
ዛሬ ጠዋት እስከ ቀትር ድረስ ከጎንደር አምባጊዮርጊስ የሚወስደው መንገድ ተዘግቶ ነበር።
ለ3ቀናት ለተጠራው አድማ ምላሽ እንደሆነ በተገለጸው በዚሁ መንገድ የመዝጋት ተቃውሞ ተሽከርካሪዎች ለሰዓታት ቆመው እንደነበረ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከባህርዳርና ጎንደር ወደ አዲስ አበባና አጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች የሚያመሩ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶቡሶች በአድማው ምክንያት ከጉዟቸው መቅረታቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ዛሬ ከባህርዳር የተነሱ 3 የአባይ ባስ አውቶብሶች ከቡሬ ተመልሰው መንገዶኞቻቸውን ማራገፋቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የስካይ ባስና የጎልደን ባስ አውቶብሶችም ጉዟቸውን አቋርጠው ተመልሰዋል።
አንደኛ ደረጃ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶች ይጓዙ ከነበረበት ስምሪት እየተመለሱ መንገደኞቻቸውን ማውረዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ከህዝብ ማመላሺያ አውቶብሶች በተጨማሪ የተለያዩ ጭነት የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችም ስራ አቁመው መዋላቸው ታውቋል።
በተያያዘ ዜናም ከባህርዳር ወደተለያዩ ከተሞች ጉዞ ሲያደርጉ የነበሩ የሰላም ባስ አውቶቡሶች መንገደኞቻቸውን በማውረድ ባህርዳር የወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንዲያድሩ መደረጋቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
ሌሎቹ አውቶብሶች በመደበኛ የማደሪያ ቦታቸው ሲቆሙ፣ ጥቃት ይደርስባቸዋል በሚል ሰላም ባስ አውቶብሶችን በወታደራዊ ካምፕ እንዲያድሩ መደረጋቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ወደ ሱዳን የሚወስደው መንገድ ላይ የአገዛዙ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
መንገዱ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች በሚወሰድ ርምጃ ለጉዞ አደገኛ በሚል በአገዛዙ የተፈረጀ መሆኑም ታውቋል።
አዲስ ዘመን፣ እብናት ፣ ጎንደር አካባቢ ያሉ መንገዶችም ውጥረት የነገሰባቸው ሲሆን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጭር ብለው መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በባህርዳር ከተማ አድማ ሊካሄድ ይችላል በሚል ስጋት በርካታ የፌደራል ፖሊሶች ከወትሮው በተለየ ቁጥጥር እያደረጉ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተመሳሳይ ወደጎንደር በርካታ ወታደሮች ተንቀሳቅሰዋል ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አስተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ወጣቶች ካለፉት 5 ቀናት ጀምሮ እየታደኑ ሲታሰሩ እንደነበር ወጣቶች ተናግረዋል። በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ በመሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጎንደር ጯሂት በተሰኘ ወረዳ በአገዛዙ ታጣቂዎች ላይ ርምጃ መወሰዱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት በፌደራልና በጸረ ሽምቅ ሃይል አባላት ላይ ግድያ የተፈጸመ ሲሆን 10 የሚሆኑት መገደላቸው ታውቋል።
በሌላ በኩልም በደባርቅና ዳባት ውጥረት መንገሱን ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ አጠቃላይ አመጽ እንዳያመራ የአገዛዙ ታጣቂዎች በብዛት እንዲሰማሩ መደረጋቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.